አዲስ አበባን ጨምሮ በአራት ክልሎች የደም እጥረት አጋጥሟል ተባለ
በአዲስ አበባ በቀን ከዚህ በፊት እስከ 450 ከረጢት ደም ይሰበሰብ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ እየተሰበሰበ ያለው ከ300 ከረጢት በታች ነው ተብሏል
ጦርነት ባለባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎች የደም ዕጥረቱ አላጋጠመም ተብሏል
አዲስ አበባን ጨምሮ በአራት ክልሎች የደም እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ፡፡
የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት እንዳስታወቀው አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሶማሌ ክልሎች በህክምና ተቋማት የደም እጥረት አጋጥሟል፡፡
በአዲስ አበባ ከዚህ በፊት በቀን እስከ 450 ከረጢት ደም ከበጎ ፈቃደኞች ይሰበሰብ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ እየተሰበሰበ ያለው ግን ከ300 ከረጢት ደም በታች ነው እንደ ባንኩ ገለጻ፡፡
ለ80 አካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ አካል በነጻ የሰራው በጎ ፈቃደኛ
አዲስ አበባ ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች ከባድ የሚባሉ የህክምና አገልግሎቶች የሚሰጡበት ቦታ መሆኑ የደም እጥረቱን ከፍተኛ አድርጎታል፡፡
ባንኩ ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ደም በመሰብሰብ ለህክምና ተቋማት በነጻ የሚሰጥ ሲሆን ህክምና ፈልገው ወደ ጤና ተቋማት ለሚመጡ ታካሚዎችም ይሰጣል፡፡
ይሁንና በአራቱ ክልሎች በተለይም የካንሰር ህሙማንን፣ ወላድ እናቶችን፣ የድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎችን እና ሌሎች ህክምና ፈላጊዎችን ለማከም የደም እጥረት እንዳጋጠመ በባንኩ የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ተመስገን አበጀ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ተመስገን መረጃ ከሆነ ከካንሰር እና ሌሎች ታማሚዎች የሚፈስን ደም ማስቆም የሚችለውን ደም (ፕላት ሴል) ለመስጠት በአዲስ አበባ ብቻ በቀን 200 ፕላት ሴል ያስፈልጋል፡፡
እንደ ዶ/ር ተመስገን ገለጻ በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች የደም እጥረት ያጋጠመው ትምህርት ቤቶች ዘግይተው በመከፈታቸው እና ክረምት ወራት ላይ ደም ይለግሱ የነበሩ በጎ ፈቃደኞች አሁን ላይ መልሰው ደም ለመለገስ ሶስት ወራትን መጠበቅ ስላለባቸው ነው፡፡
የጦርነት ቀጠና በሆነው በሰሜን ኢትዮጵያ የደም እጥረት አላጋጠመም ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “አካባቢው የጦርነት ቀጠና እንደመሆኑ መጠን የተጎጂዎች ቁጥር ስለሚጨምር የደም ፍላጎት ይጨምራል ይሁንና በአፋር እና በአማራ ክልሎች በጎ ፈቃደኞች በፍላጎቱ ልክ ደም እየለገሱ በመሆኑ እስካሁን የደም እጥረት አላጋጠመም” ብለዋል ዶ/ር ተመስገን፡፡
የትግራይ ግጭትን የተመለከተው የተመድ እና የኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት ጥቅምት 24 ይፋ ይሆናል ተባለ
ብሄራዊ የደም ባንክ በአገር አቀፍ ደረጃ 43 የደም ባንክ ቢሮዎች ያሉት ሲሆን በአማራ ክልል ደሴ፣ ደብረታቦር፣ ጎንደር እና መተማ እንዲሁም በአፋር ክልል ያሉት ሰመራ እና አዋሽ ቅርንጫፎች በአካባቢው ያሉትን በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች በማስተባበር የደም ፍላጎቱን በማሟላት ላይ መሆናቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከበጎ ፈቃደኞች የሚሰበሰበው ደም በተለይም ለካንሰር ታማሚዎች እና ለሌሎች የደም መፍሰስ ላጋጠማቸው ታካሚዎች የሚያስፈልገው ፕላት ሴል የሚቆየው ለአምስት ቀናት ብቻ በመሆኑ እጥረቱ ከፍተኛ ነው እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡
በመሆኑም በጎ ፈቃደኞች በየአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የደም ባንኮች በመሄድ ደም እንዲለግሱ ዶ/ር ተመስገን አሳስበዋል፡፡