ህወኃት ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እኩል የግንባሩን ሃብት ሊካፈል እንደማይገባ ብልጽግና አስታወቀ፡፡
ህወኃት ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እኩል የግንባሩን ሃብት ሊካፈል እንደማይገባ ብልጽግና አስታወቀ፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ አወሉ አብዲ እኩል ሳናዋጣ እኩል ልንከፋፈል አንችልም ብለዋል፡፡
ድርጅቶቹ ባላቸው የአባላት ቁጥር ልክ ለግንባሩ ፈሰስ ያደርጉ እንደነበር ያስታወሱት ቃል አቀባዩ የህወኃት የአባላት ቁጥር ከሌሎቹ ያነሰ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
“መቶ ምናምን ሺ አባላት ያሉት ህወኃት ከ3 ሚሊዬን የሚበልጥ አባላት ካሉት ኦህዴድ ልክ ሊካፈል አይገባም” ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
አቶ አወሉ እንደሚሉት ድርጅቶቹ የስራ አስፈጻሚና ሌሎችንም የስልጣን ቦታዎች እኩል ተጋሩ እንጂ እኩል የአባላት ቁጥር የላቸውም፡፡
የቀድሞዎቹ አዴፓ/ብአዴን እና ደኢህዴን በቅደም ተከተል ከህወኃት የበለጠ የአባላት ቁጥር እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
ትግራይን መሰረት አድርጎ የሚታገል የትግራይ ብልጽግና ቅርንጫፍ መቋቋሙን የሚያስታውሱት አቶ አወሉ ” “እንዲያውም ቅርንጫፉ ከህወኃት ድርሻ ላይ ይገባዋል ባይ ነን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ደግሞ የቅርንጫፉ አመራሮች የራሱ የህወኃት አመራሮች የነበሩ መሆናቸውን ነው በምክንያትነት የሚያስቀምጡት፡፡
እንደቃል አቀባዩ ገለጻ ከሆነ ብልጽግና “እኩል ልንከፋፈል አይገባም” የሚለውን ይህንኑ ቅሬታውን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስገብቷል፡፡
ህወኃት ግን ይህንን የብልጽግናን ሃሳብ ይቃወማል፡፡
በተመሳሳይ ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት በህወኃት ጽ/ቤት የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊው አቶ ነጋ አሰፋ ሃሳቡን ተችተዋል፡፡
ኢህአዴግ በአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት እንዲሁም በያዘው ፕሮግራም እንጂ በህዝብም ሆነ በአባላት ቁጥር ግንባር ሆኖ አልተዋቀረም ብለዋል፡፡
ሀገር ለመምራት የሚያስችል የዓላማ አንድነት የነበራቸው ብሄራዊ ድርጅቶቹ፣ የቁጥር ልዩነት ሳያስፈልጋቸው በስራ አስፈጻሚም ሆነ በምክር ቤት እኩል ሆነው ሲሰየሙ ውሳኔዎችንም ሲያሳልፉ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
የግንባሩ መተዳደሪያ ህገ-ደንብ ይህንኑ እንደሚልና አሁን ጥያቄ የሚያነሱ ብሄራዊ ድርጅቶች ይህንኑ አምነውና ተቀብለው መግባታቸውን እስከ ሀዋሳው የግንባሩ የመጨረሻ ጉባዔ ድረስም በዚሁ መንገድ በጋራ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም ነው የተናገሩት፡፡
ከተሃድሶ በኋላም ቢሆን እያንዳንዱ 25 ሚሊዬን ብር ያዋጡ እንደነበር ነው አቶ ነጋ የሚናገሩት፡፡
ሆኖም “ሁሉም እኩል ሲያዋጡ እና ገቢ ሲያደርጉ ነበር ወይ?” ሲሉ የሚጠይቁት ኃላፊው ከመዋጮው አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ያላቸውን ቅሬታ ለቦርዱ ሊያስገቡ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት፡፡
ክፍፍሉን በተመለከተ የቦርዱ ውሳኔ ትክክል ነው ያሉም ሲሆን “ውሳኔን አልቀበልም ማለት ማን አለብኝነት ነው ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የብልጽግና የትግራይ ቅርንጫፍ ከህወኃት ድርሻ ሊካፈል ይገባል መባሉንም አጥብቀው ኮንነዋል፡፡ “ሀሳቡ ፍጹም ወንጀል ነው” ሲሉም ነው ተቃውሟቸውን የገለጹት፡፡
የሦስቱን ብሄራዊ ድርጅቶች ውህደት ህጋዊ ነው ብሎ የማያምነው ህወኃት ኢህአዴግ የሚጨፈለቅ አይደለም በሚል በስራ አስፈጻሚና በማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በጉባዔው ጭምር ላለመዋሃድ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ሆኖ ሳለ “ከየት እንደተሰበሰቡ የማይታወቁ ተሰብስበው ቢዋሃዱና ብልጽግና ነን ቢሉ አይመለከተንም ” ብለዋል፡፡
ብልጽግና አስገባሁ ያለውን ቅሬታ በተመለከተ የደረሳቸው ነገር እንደሌለ የገለጹም ሲሆን የቦርዱን ውሳኔ አይተው የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡም አስታውቀዋል፡፡
የኢህአዴግን መፍረስ በይፋ የወሰነው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ “ከእዳ ክፍያ ቀሪ የሆነ ሃብት 3/4ኛው ለብልጽግና ፓርቲ (የሶስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት በመሆኑ) ¼ኛ ደግሞ የህወሃት ድርሻ መሆኑ ታውቆ በዚያ መሰረት ክፍፍል እንዲያጠናቅቁና ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በህጉ መሰረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ” ሲል በቅርቡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ቅሬታውን ተከትሎ የቦርዱን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
በተሳካልን ጊዜ ምላሹን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል፡፡