በኢትዮጵያ 12ኛ ክልል እንዲቋቋም የሚያስችል ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የፌዴሬሽን ም/ቤት ወሰነ
የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ በነበሩበት ክልል ይቀጥላሉ ተብሏል
ምክር ቤቱ በክልል የመደራጀት ጥያቄዎችን ለመመለስ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ወስኗል
በኢትዮጵያ 12ኛ ክልል እንዲቋቋም የሚያስችል ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ አሳለፈ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤው በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይኖሩ የነበሩ የ6 ዞኖችና የ5 ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ ክልል የእንደራጅ አቤቱታ ላይ መክሯል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከለውጡ በፊት በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው ለግጭት መንስዔ ሲሆኑ ቆይተዋል ብለዋል።
ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እንሁን ጥያቄዎችን በህዝበ ውሳኔ እንዲቋቋሙም አድርጓል።
ምክር ቤቱ በዛሬው የአስቸኳይ ጉባኤ
የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ ''የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል'' የመመስረት ጥያቄ ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/3 እና ከምክር ቤቱ ደንብ ቁጥር 4/2014 አንቀጽ 19/2 አንጻር ውሳኔ ለመስጠት እንዲያስችል የሕዝብን ይሁንታ ማረጋገጥ ስለሚያስፈልግ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ በሆነ መልኩ ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥ አጽድቋል።
ህዝበ ውሳኔውን ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ እንዲያከናውን የወሰነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ የሕዝብ ውሳኔው ውጤት ሪፖርት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲቀርብለትም አሳስቧል።
እንዲሁም የሕዝብ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና የሕዝብን ሰፊ ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ ወስኗል።
በምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረትም የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ እንደሚቀጥሉም አስታውቋል።
የጉራጌ ዞን ከሀዲያ፤ ከስልጤ፣ ከከንባታ ጠንባሮና ከየም ልዩ ወረዳ ጋር በክላስተር ተደራጅቶ ክልል እንዲሆን የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
የጉራጌ ዞን፤ የዞኑ ምክር ቤቱን ከሰሞኑ ከክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ያሳለፈውን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስገባቱንም አስታውቋል።