የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓትን ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አገደ
ህወሓት በሶስት ወራት ውስጥ “የእርምት እርምጃ” ካልወሰደ ይሰረዛል ሲል ቦርዱ አስጠንቅቋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/13/252-174019-whatsapp-image-2025-02-13-at-4.39.45-pm_700x400.jpeg)
ህወሓት ላለፉት ወራት ለሁለት ተከፍሎ እሳጣ ገባ ውስጥ መግቱ ይታወቃል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማገዱን አስታወቀ።
ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ለቀጣይ ሶስት ወራት “በምንም አይነት” ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ማገዱን አስታውቋል።
ቦርዱ ፓርቲው በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ፤ የጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሄድ፣ መተዳደሪያ ደንቡን ሳያፀድቅና አመራሮቹን ሳይመርጥ በሕግ የተሰጠው የስድስት ወር ጊዜ በመጠናቀቁ ነው ለመታገዱ ምክንያት መሆኑን አሰታውቋል።
ቦርዱ “ህወሓት በልዩ ሁኔታ ተመዝግቦ አንደሚንቀሳቀስ ፓርቲ ምርጫ ቦርድን ሕግ፣ መመሪያና ውሣኔዎችን አክብሮ መንቀሳቀስ ሲገባው በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀፅ 3(11) (ሀ) እና ዐዋጁን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ አንቀጽ 16(6) ሲጥስ ተገኝቷል” ብሏል።
በዚህም መሰረት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለቀጣይ ሶስት ወራት ከማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መታገዱን ነው ቦርዱ ያስወቀው።
ፓርቲው ለእግዱ ምክንያት የሆነውን ጥሠት በማረም፤ ዐዋጁን፣ ዐዋጁን ተከትሎ የወጣውን መመሪያ፣ የቦርዱን ውሣኔዎችና ትዕዛዞች በማክበር ፓርቲው ሊያደርግ የሚገባውን ጠቅላለ ጉባዔ ለማድረግ የሚያስችለውን የጉባዔ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት ለቦርዱ በጽሑፍ ሲያሳውቅና ቦርዱ ይህንኑ ሲያረጋግጥ በመመሪያው አንቀጽ 18(2) መሠረት ቦርዱ ዕግዱን የሚያነሣ መሆኑንም አስታውቋል።
ህወሓት በቀጣይ 3 ወራ ጊዜ ውስጥ “የእርምት እርምጃ” ካልወሰደ፤ የፓርቲው ምዘገባ በቀጥታ እንደሚሰረዝ ቦርዱ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ በነሐሴ 2016 ዓ.ም ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት “በልዩ ሁኔታ” መስጠቱ ይታወሳል።
ህወሓት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ በፓርቲነት መመዝገቡን ተከትሎ የቦርዱን ውሳኔ እንደማይቀበለው ማስታወቁ ይታወሳል።
ፓርቲው ህጋዊ ሰውነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ጠየኩት ማለቱም አይዘነጋም።