ህወሓት የጠራውን ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አይችልም - ምርጫ ቦርድ
ቦርዱ ባወጣው መግለጫ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ከማድረጉ ከ21 ቀን በፊት ሊያሳውቀኝ ይገባ ነበር ብሏል
14 የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በፓርቲው ጉባኤ እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸው ይታወሳል
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የጠራው ጠቅላላ ጉባኤው ሊካሄድ አይችልም አለ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ።
ቦርዱ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ መጥራቱን በመገናኛ ብዙሃን መመልከቱን ጠቅሶ ይሁን እንጂ ፓርቲው ለቦርዱ ስለጉባኤው አለማሳወቁን ጠቁሟል።
ህወሓት ከነሃሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን ቦርዱ በመግለጫው አውስቷል።
በዚህም መሰረት ፓርቲው የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ከደረሰው ጀምሮ በቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅና እነዚህን አዋጆች መሰረት ተደርገው በወጡ መመሪያዎች እና የቦርዱ ውሳኔዎች መሰረት ይተዳደራል ብሏል።
ቦርዱ ውሳኔ የሰጠባቸውና በደብዳቤው ከገለፃቸው በፓርቲው መተግበር ካለባቸው ተግባራት መካከል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ከማድረጉ ከ21 ቀን በፊት ለቦርዱ ማሳወቅና ፓርቲው በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባዔ የቦርዱ ታዛቢዎች መገኘት አለባቸው የሚሉት በዋናነት የተገለፁ ግዴታዎች መሆናቸውንም ነው ያነሳው።
ይሁን እንጂ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ሊያደርግ መሆኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየተዘገበ መሆኑ ተረድቻለሁ ያለው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፥ ቦርዱ ባላወቀበትና ቅድመ ዝግጅት ባልተደረገበት እንዲሁም ታዛቢዎች ባልተገኙበት ሁኔታ የተጠራው ጉባኤው ሊካሄድ እንደማይችል አስታውቋል።
ጠቅላላ ጉባኤው ከቦርዱ ፍቃድ ውጭ ከተካሄደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዚህ ጉባዔም ሆነ በጉባዔዎቹ ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ ዕውቅና እንደማይሰጥ ነው በመግለጫው የገለጸው።
ህወሓት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ በፓርቲነት መመዝገቡን ተከትሎ የቦርዱን ውሳኔ እንደማይቀበለው ማስታወቁ ይታወሳል።
ፓርቲው ህጋዊ ሰውነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ላቀረበው ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ የተቃወመበትን መግለጫ ባወጣ ማግስት ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቷል።
14 የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም ከምዝገባ ጋር በተያያዘ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ያለው ችግር ሳይፈታ ጉባኤ መጥራት ተገቢ አይደለም በሚል ከጉባኤው ራሳቸውን ማግለላቸውን ማሳወቃቸው አይዘነጋም።