ምርጫ ቦርድ ህወሓትን "በልዩ ሁኔታ" በፓርቲነት መመዝገቡን በትናንትናው እለት ማስታወቁ ይታወሳል
ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ላቀረበው የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ እንደማይቀበል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሀምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የቀረበለትን የተሰረዘውን የህወሓት ህጋዊ ሰውነት ወደ ነበረበት የመመለስ ጥያቄ ተከትሎ፤ በነሓሴ 03 ቀን 2016 ዓ.ም ህወሓት በልዩ ሁኔታ የተመዘገበ መሆኑን ስለማሳወቅ” የሚል አርእስት የተሰጠው የቦርዱን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ እንደደረሰው አስታውቋል።
ህወሓት ያቀረበው ጥያቄ ከፕሪቶሪያው ስምምነት፣ ከህግ እና ህወሓት እያደረገ ካለው ተጨባጭ እንቅስቃሴ አንፃር የተሰረዘውን ህጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ የሚል ብቻ ነው ብሏል።
ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ህጋዊ ሰውነቱን ለመመለስ ሰለማያስችል ህውሓት ህጋዊ ሰውነቱን በሚያገኝበት ሁኔታ ላይ የፓርቲው የስራ ሀላፊዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት የስራ ሀላፊዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማካሄድ የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ነው ያታወሰው።
በዚህ መሰረት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰውነቱን ወደነበረበት እንዲመለስለት ብቻ በሀምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ጥያቄእንዳቀረበ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
ሆኖም ቦርዱ የፕሪቶሪያውን ስምምነት፣ ከዚህ በፊት በሌሎች የፌደራል ተቋማት የተሰጡትን ውሳኔዎች፣ ሌሎች ህጎች እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረሱ መግባባቶች ወደጎን በመተው መፍትሄን ያላገናዘበ ጥያቄው ሌላ መልሱ ሌላ' የሆነ የውሳነኔ ሀሳብ ማሳለፉ ተገቢ አይደለም ሲል ቅሬታውን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ከፓርቲው ጥያቄ እና እውቅና ውጪ በፍትህ ሚኒስቴር የተፃፈውን ደብዳቤ በአባሪነትና መነሻነት ጠቅሷል ሆኖም የፍትህ ሚኒስቴሩ ደብዳቤ ከፍ ብሎም እንደተገለፀው በህወሓት በኩል ምንም ዐይነት ጥያቄ ሳይቀርብና ከህወሓት እውቅና ውጪ የተፃፈ በመሆኑ በይዘቱም እንደማይሳማ አስታውቋል።
ህወሓት በምርጫ ቦርድ የልዩ ፓርቲ ምዝገባ ላይ እንደተገለጸውም የተሰረዘውን ህጋዊ ሰውነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ የሚያግዙ ሰነዶች ማለትም የፓርቲው ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ እና የጠቅላላ አመራሮቹ ዝርዝር የያዘ ሰነድ እንጅ በማሻሻያ አዋጁ መሰረት የስራ አስፈፃሚ አባላት ስም፣ አድራሻ እና በተለየ ሁኔታ ሀላፊነት ወስደው ቃል የሚገቡበትን የተፈረመ ሰነድ ለቦርዱ አላቀረብኩም ብሏል።
በዚህም በቦርዱ ውሳኔ ላይ የተካተቱት ዝርዝር ይዘቶች አዲስ በወጣው ማሻሻያ ህግ መሰረት የተቀመጡና ህወሓት ካቀረበው ጥያቄ ጋር የማይገናኙ ናቸው ያለው ፓርቲው፤ ድርጅቱ ህጋዊ ሰውነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ያቀረበውን ጥያቄ የማይመልስ በመሆኑ የቦርዱን ውሳኔ እንደማይቀበለው በይፋ አቋሙን ገልጿል።
ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ውሳኔው በፕሪቶሪያው ስምምነት ያልተመሰረተ፣ ከዚህ በፊት በሌሎች የፌደራል ተቋማት የተሰጡትን ውሳኔዎች እንዲሁም የነበሩ ውይይቶችን የሚቃረኑ ዝርዝር ይዘቶች በህወሓት ላይ የሚጭን መሆኑን በመግለጽ የቀረበው ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ የፓርቲው ሕገ ደንብ በሚፈቅድለት መልኩ ተያያዥ ስራዎች እንደሚያከናውን እና የፌደራል መንግስቱም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትና የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ምርጫ ቦርድ ህወሓትን "በልዩ ሁኔታ" በፓርቲነት መመዝገቡን መቃወማቸው ይታወቃል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ለምርጫ ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ ቀርቧል የተባለውን የምዝገባ ጥያቄ ህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለነዝህ ግለሰቦች የሰጠው ምዝገባ በተጭበረበረ ማስረጃ መሰረት የተሰጠ በመሆኑ መልሶ እንዲመረምረው እንጠይቃለን” ብለዋል።