የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ
ከኃላፈነታቸው የለቀቁበት ምክንያትም “ጤናዬን በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት የሚያስፈልገኝ” ነው ብለዋል
ወ/ሪት ብርቱካን “በገዛ ፍቃዴ መልቀቄን ለተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ ጽህፈት ቤት ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም አሳውቄያለሁ” ብለዋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ከኃላፊነታቸው በራሳቸው ፈቃድ መልቀቃቸውን አስታወቁ።
ወ/ሪት ብርቱካን በማህበራዊ ትስስር ገጻው በሳፈሩት ጽሁፍ፤ “ጤናዬን በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት የሚያስፈልገኝ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብለዋል”
በዚህም “ከነሀሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ሰብሳቢነቴ በገዛ ፍቃዴ መልቀቄን ለተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ጽህፈት ቤት ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም አሳውቄያለሁ” ሲሉም ገልጸዋል።
“በሚቀረኝ ጊዜ ያልተጠናቀቁ ስራዎችን የማጠናቀቅ እና አስተዳደራዊ ሽግግር የመፈፀም ሃላፊነቶችን የምወጣበት ይሆናል” ሲሉም አስታውቀዋል።
- “የጊዜ ጉዳይ ነው እንጅ ጥሩ ምርጫ ማድረጋችን አይቀርም” የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን
- “በመጪው ምርጫ ተመጣጣኝ ውክልና ስርዓትን ለመተግበር እንቸገራለን” ብርቱካን ሚዴቅሳ
ወ/ሪት ብርቱካን “ባለፉት 4 አመት ከ6 ወራት የምርጫ ቦርድን የማስፈጸም አቅምን ለመጨመር፣ ተአማኒነቱን ለማሳደግ ከሌሎች የቦርዱ አመራር አባላትና ከቦርዱ ሰራተኞች ጋር በጋራ ለፍተናል” ብለዋል።
“በእኔ በኩል የቦርዱን ተአማኒነት በማሻሻል ረገድ፣ በተቻለ አቅምም የፓለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴዎች ለማገዝ ባደረግነው ጥረት ስኬታማ ነን ብዬ አምናለሁ”ሲሉም ገልጸዋል።
የቦርድ አመራር አባላትን፣ የቦርዱን ሰራተኞች እንዲሁም የፓለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእጩነት ስላቀረቧቸው እንዲሁም ኃፊነቱን ለሰጣቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በ2011 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ ነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በመሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሸመው ስራ የጀመሩት።
በሃላፊነት ላይ በነበሩባቸው 4 ዓመት ከስድስት ወራት አንድ ሀገራዊ ምርጫ እንዲሁም ሶስት ህዝበ ውሳኔዎችን መምራት ችለዋል።