አቶ ልደቱ በ30 ሺ ብር ዋስትና ከእስር ተለቀው ቤታቸው መግባታቸውን ፓርቲያቸው ገልጿል
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያው ፓርቲ (ኢዴፓ) መስራችና የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው ከ140 ቀናት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ከእስር መለቀቃቸው ተሰማ፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ምስራቅ ምድብ ችሎት አቶ ልደቱ በ30 ሺ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ እና ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ በወሰነው መሰረት ነው ከእስር የተለቀቁት፡፡ አቶ ልደቱ ከእስር ቤት ወጥተው ወደ ቤታቸው መግባታቸውን አል አይን ከኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ አረጋግጧል፡፡
ከዚህ ቀደም የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት "ሕገወጥ የጦር መሳርያ ይዞ መገኘት" በሚል የተከፈተባቸውን ክስ በ አንድ መቶ ሺህ ብር ዋስትና በውጪ ሆነው እንዲከታተሉ የፈቀደላቸው ቢሆንም ፖሊስ ሳይለቃቸው በማቆየት ሁለተኛው ክስ እንደመሰረተባቸው ፓርቲው ገልጿል፡፡ ቀጣይ የክስ ሂደታቸውን ለመከላከል አቶ ልደቱ ለታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም እንደተቀጠሩ እና በቀኑ ክርክሩ እንደሚቀጥል አቶ አዳነ ታደሰ ገልጸዋል፡፡
አቶ ልደቱ የ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ የተቀሰቀሰውን የወጣቶች አመጽ አስተባብረዋል በሚል ከታሰሩ ዛሬ አንድ መቶ አርባ ቀናት እንደሞላቸው ኢዴፓ በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል፡፡