አቶ ልደቱን ለማስፈታት የተወሰነውን የዋስትና ሂደት እያስፈጸመ መሆኑን ኢዴፓ ገለጸ
አቶ ልደቱ የከፈተባቸውን ክስ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል
አቶ ልደቱ በ30 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ወስኗል
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያው ፓርቲ (ኢዴፓ) መስራችና የፓርቲው ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው በ30 ሺ ብር ዋስ እንዲወጡ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ምስራቅ ምድብ ችሎት ወሰነ፡፡
የኦሮሚያ ዓቃቤ ህግ "የፌዴራልና ክልል መንስታትን ማፍረስ" በሚል የከፈተባቸውን ክስ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉም ነው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ምስራቅ ምድብ ችሎት ዛሬ ጠዋት በዋለው ችሎት የወሰነው፡፡
የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለአል-ዐይን እንደገለጹት በአሁኑ ሰዓት ለዋስትና የሚያዘውን 30 ሺህ ብር በመክፈል አቶ ልደቱን ለማስፈታት የሚያስፈልጉ ሂደቶች እየተከናወኑ ነው፡፡ ሂደቱ አልቆ ከሰዓት በኋላ ሊለቀቁ እንደሚችሉም አቶ አዳነ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት፣ "ሕገ-ወጥ የጦር መሳርያ ይዞ መገኘት" በሚል የተከፈተባቸውን ክስ በመቶ ሺህ ብር ዋስትና በውጪ ሆነው እንዲከታተሉ የፈቀደላቸው ቢሆንም ፖሊስ ሳይለቃቸው በማቆየት ሁለተኛውን ክስ እንደመሰረተባቸው ይታወቃል፡፡
“አሁንስ ከእስር እንደሚለቀቁ ምን ያክል እርግጠኛ ናችሁ?” በሚል ለአቶ አዳነ ላነሳንላቸው ጥያቄ “ውሳኔው የተሰጠው የኦሮሚያ ዓቃቤ ህግም አቶ ልደቱ ውጭ ሆነው የክስ ሂደታቸውን ቢከታተሉ እንደማይቃወም ከገለጸ በኋላ በመሆኑ እንደሚፈቱ በእርግጠኝነት መግለጽ ይቻላል” ብለዋል፡፡
ቀጣይ የክስ ሂደታቸውን ለመከላከል አቶ ልደቱ ለታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም እንደተቀጠሩ እና በቀኑ ክርክሩ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
አቶ ልደቱ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ የተቀሰቀሰውን የወጣቶች አመጽ አስተባብረዋል በሚል ከታሰሩ ዛሬ አንድ መቶ አርባ ቀናት እንደሞላቸው ኢዴፓ በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል፡፡