ለሀገር ስጋት ችግር ይፈጥራል ያለውን ጉዳይ በየትኛውም፤ በማንኛውም ሰዓት ንጹሃን ዜጎችን በጠበቀ መልኩ ሊመታ እንደሚችል ገልጸዋል
ዛሬ በሰሜን ኢትዮጵያ መቀሌ ከተማ የአየር ድብደባ መከናወኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መቀመጫቻን መቀሌ ያደረጉ የተራዲኦ ድርጅቶች ሰራተኞችን ምንጭ በማድረግ እየዘገቡ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም በከተማዋ የአየር ድብደባ እንደተፈጸመ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጃቸው የህወሃት አመራሮች በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጉዳዩን እየተነጋገሩበት ነው፡፡
አንዳንዶች በመቀሌ ከተማ የኢትዮጵያ አየር ሀይል ድብደባ መፈጸሙንና ወሳኝ የህወሓት የጦር ማከማቻዎችን እና መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ አጠገብ ያለን ዴፓን መደብደቡን እየጻፉ ናቸው፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ አል ዐይን ኒውስ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ጋር የሥልክ ቆይታ አድርጓል፡፡ ዶ/ር ለገሰ እንደገለጹት መንግስት የራሱን ከተማ በምን ምክንያት ይበድባል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የራሱ ዜጎች የሚኖሩበትን ከተማ እንዲሁም የራሱን ዜጎች ሊያጠቃ የሚችልበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ሚኒስትሩ ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቀዋል፡፡ ህወሃት በአጠቃላይ የምዕራቡ ዓለም መንግስት ላይ ጫና ይፈጥርልኛል ብሎ ቀደም ሲል፤ በአየር እና በምድር እየደበደበኝ ነው ሲል የነበረው ለማጠናከሪያ እና ለማሳሳት የተጠቀመበት እንደሆነ ገልጸዋል።
መንግስት ለሀገር ስጋት ችግር ይፈጥራል ያለውን ጉዳይ በየትኛውም ፤ በማንኛውም ሰዓት ንጹሃን ዜጎችን በጠበቀ መልኩ ሊመታ እንደሚችል የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ደግሞ መንግስት ማንንም ማስፈቀድ እንደማይጠበቅበት ተናግረዋል።