በትግራይ ያለውን ሰብዓዊ አቅርቦት ለማቀላጠፍ በሚል የፍተሻ ጣቢያዎች ቁጥርን መቀነሱን መንግስት አስታወቀ
ወደ ክልሉ ከገቡ 466 ተሽከርካሪዎች 428ቱ አለመመለሳቸው እንዳሳሰበውም ነው መንግስት የገለጸው
በአሁኑ ሰዓት በሰመራም ሆነ በሌሎች የፍተሻ ጣቢያዎች የቆመ ተሽከርካሪ እንደሌለም አስታውቋል
በትግራይ ክልል የሚቀርቡ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማቀላጠፍ በሚል የፍተሻ ጣቢያዎችን ቁጥር መቀነሱን መንግስት አስታወቀ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሰመራም ሆነ በሌሎች የፍተሻ ጣቢያዎች የቆመ ተሽከርካሪ እንደሌለም አስታውቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ሳምንታዊ የስራ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክረታሪ ቢልለኔ ስዩም ትናንት ሃሙስ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
መግለጫው በዋናነት እስከ መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ/ም ስለነበሩ ሰብዓዊ እንቅስቃሴዎች ያተኮረ ነው፡፡
በመግለጫቸው ሰብዓዊ አቅርቦቶችን ለማቀላጠፍ እየተሰሩ ስላሉ ያነሱት ፕሬስ ሴክረታሪዋ በትግራይ የሚደረገውን ሰብዓዊ አቅርቦት ለማሳደግ በማሰብ የፍተሻ ኬላዎች ቁጥር ከ7 ወደ 2 ዝቅ እንዲል መደረጉን ገልጸዋል በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን በመጠቆም።
ይልቁንም የእርዳታ ተቋማቱ እናሰማራለን የሚሉት የተሽከርካሪዎች ቁጥር ጭማሪ አለማሳየቱን ነውፕሬስ ሴክሬታሪዋ የገለፁት። ፡፡
ምግብ ነክ ያልሆነ ከ6 ሺ ቶን በላይ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ከ50 ሺ በላይ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ በላይ ቀርቧል ያሉም ሲሆን 760 ሺ ሊትር ገደማ ነዳጅ እንዲሁም ከ1 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርጥ ዘር መቅረቡንም አስታውቀዋል፡፡
የእርዳታ በረራዎች ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ እንደሚደረጉ እና የአውሮፓ ህብረት ሰብዓዊ በረራዎች ማድረግ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በዚህ መካከል 32 የእርዳታ ተቋማት ለስራዎቻቸው የሚሆን 144 ሚሊዮን ብር ወደ መቀሌ እንዲወስዱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ 590 ተሽከርካሪዎችም በክልሉ ተሰማርተዋል፡፡ ሆኖም የአብዛኞቹ ተሽከርካሪዎች አለመመለስ ጥያቄን የሚያጭር እና እርዳታዎችን በሌሎች አካባቢዎች ለማቅረብ እክል የሚፈጥር እንደሆነ ነው ቢልለኔ የገለጹት፡፡
“በዋናነት አንድን የእርዳታ ተቋም የሚመለከት ቢሆንም ወደ ክልሉ ከገቡ 466 ተሽከርካሪዎች 428ቱ ገና ተመልሰው አልወጡም፤ ይህ 40 ያህሉ ተሽከርካሪዎች ብቻ መመለሳቸውን የሚያሳይ ነው”ም ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)ም ይህ ሁኔታ እንዳሳሰበው ትናንት በኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ቢሮው በኩል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት መቀሌ ከደረሱ 149 የርዳታ ተሽከርካሪዎቹ መካከል የተመለሰ እንደሌለ ያስታወቀው ቢሮው ከወርሃ ሃምሌ መባቻ ጀምሮ እርዳታዎችን ጭነው ወደ ትግራይ ከገቡ 466 ተሽከርካሪዎች 38ቱ ብቻ መመለሳቸውን በማስታወስ ሁኔታው እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡
ተሽከርካሪዎቹ በክልሉ የህይወት አድን እርዳታዎችን ለማቅረብ እንደሚፈለጉም ነው የገለጸው።
ብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር እስካሳለፍነው መስከረም 4 ድረስ ከ6 የአፋር ክልል ወረዳዎች ለተፈናቀሉ ከ70 ሺ በላይ ሰዎች 10 ሺ ኩንታል ምግብን አሰራጭቷል፡፡
በጥቅምት ወር በክልሉ የሚቀርበው ምግብም ተገኝቷል ብለዋል እርዳታው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ፕሬስ ሴክረታሪዋ፡፡
በአማራ ክልል ያለው የተፈናቃዮች ቁጥር ከ500 ሺ በልጧል፡፡ ተፈናቃዮቹ በዋናነት ከዋግኸምራ፣ ከሰሜን ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ የተፈናቀሉ ናቸው፡፡
በህወሓት ጥቃት ምክንያት ከተለያዩ የሰሜን ወሎ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ከ270 ሺ በላይ ዜጎች በደሴ ከተማ ተጠልለዋል ይገኛሉ፡፡
እስካሳለፍነው መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ/ም ድረስ ከ27 ሺ ኩንታል በላይ ምግብ ደሴ ለሚገኙት ተፈናቃዮች ቀርቦ ከ178 በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት ቢልለኔ በ9 ተሽከርካሪዎች የተጫነ 2 ሺ 670 ኩንታል ምግብ በዋግኸምራ መሰራጨቱንና እስከ ጿጉሜ 3 ቀን 2013 ዓ/ም ድረስ ደግሞ በ5 ተሽከርካሪዎች የተጫነ 1 ሺ 940 ኩንታል ምግብ በዳውንት ወረዳ ለሚገኙ የሰሜን ወሎ ተጠቃሚዎች መድረሱን አስታውሰዋል፡፡