መንግስት በተረጋጋና በተጠና ሁኔታ እርምጀ እንደሚወስድ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ
ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ጦርነቱ የማይመለከተው ሰው ስለሌለ፤ ሁሉም ወገን ከመከላከያ ጎን እንደሆን ጥሪ አቀርበዋል
በውጫሌ እና ጭፍራ አካባቢዎች፤ ህወሓት 30 ንጹሃንን መግደሉንም አስታውቋል
በአማራ ክልል ውጫሌ እንዲሁም በአፋር ክልል ጭፍራ አካባቢዎች ህወሓት 30 ንጹሃንን መግደሉን የመንግስት ቃል አቀባይ አስታወቁ።
አዲስ የተቋቋመው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የተፈረጀው ሕወሃት በውጫሌና ጭፍራ አካባቢዎች ብቻ 30 ንጹሃን መግደሉን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ፤ ህወሓት በአሁኑ ወቅት የከፈተውን ጦርነት ሁሉም ወገን ከመከላከያ ጎን ተሰልፎ እንዲመክትም ጥሪ አቅርበዋል።
ዶ/ር ለገሰ፤ ህወሓት በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ላይ ንጹሀንን እየገደለ መሆኑን ገልጸው ከሰሞኑም ቡድኑ በከባድ መሳሪያ በፈጸመው ድብደባ በውጫሌ እና ጭፍራ አካባቢዎች ንጹሀንን መግደሉን እንደቀጠለ አስታውቀዋል።
ህወሓት ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ሰሜን ዕዝን በማጥቃት እንደጀመረ ያስታወሱት ዶ/ር ለገሰ፤ ይህንን ጥቃት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ እና የአፋር ልዩ ሀይሎች መክተው አገርን ታድገዋል ብለዋል።
ህወሃት እያደረገ ያለው ጭፍጨፋ በታሪክ ይቅር የማይባል እንደሆነ ያኑሱት ሚኒስትሩ፤ ቡድኑ “ሀገር የማፍረስ ህልሙን ለማሳካት የሰው ማዕበል ስልትን እየተከተለ የትግራይ ህጻናትን እያስፈጀ ነው” ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) መንግስት በተረጋጋና በተጠና ሁኔታ እርምጀ እንደሚወስድም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
“ይሄ ጦርነት የማይመለከተው ሰው ስለሌለ አሸባሪው ህወሓት በአሁኑ ወቅት የከፈተውን ጦርነት ሁሉም ወገን ከመከላከያ ጎን በመሆን መመከት አለበት“ ሲሉም ጥሪ አቀርበዋል።