መንግስት አቶ ስብሃት ነጋና አቶ ጃዋር መሃመድን ጨምሮ የተወሱ እስረኞችን በምህረት መልቀቁን አስታወቀ
ውሳኔው ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ለሰላም ሲባል መወሰኑን አስታውቋል
ምሕረቱ ከዚህ በፊት በተፈጸመ ጥፋት የታሠሩትንም ሆነ በቅርቡ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሠሩትን ያካትታል
ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም ሲል መንግሥት የተወሰኑ እሥረኞችን በምሕረት መፍታቱን አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አግልግሎት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት፣ አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ከሚጠበቅበት ሞራላዊ ግዴታዎች አንዱ ምሕረት በመሆኑ ለተሻለ ፖለቲካዊ ምኅዳር ሲባል የተወሰኑ እሥረኞችን መንግሥት ዛሬ በምሕረት ከእሥር መፍታቱን አስታውቋል።
ይህ ምሕረት ከዚህ በፊት በተፈጸመ ጥፋት የታሠሩትንም ሆነ በቅርቡ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሠሩትን እንደሚጨምር አስታውቋል።
ከእሥር በምሕረት እንዲፈቱ የተወሰነላቸው
1. አቶ ስብሐት ነጋ
2. ወሮ ቅዱሳን ነጋ
3. አቶ ዓባይ ወልዱ
4. አቶ አባዲ ዘሙ
5. ወሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር
6. አቶ ኪሮስ ሐጎስ
7. አቶ ጁሐር መሐመድና በእርሱ መዝገብ የተከሰሱ ሁሉ
8. አቶ እስክንድር ነጋና በእርሱ መዝገብ የተከሰሱ ሁሉ
መንግሥት ይሄንን ውሳኔ ሲወስን ዓላማው የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልክና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በሀገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ ለመክፈት እንሆነም ግልፅዋል።
በተጨማሪም የሕዝብን ጥያቄዎች ከግምት በማስገባትና ምንጊዜም ለሰላማዊ ፖለቲካ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት እንደሆነም አስታውቋል።
መንግሥት ይሄንን ውሳኔ በአንድ በኩል ሲወስን በሌላ በኩል ደግሞ ያለፉ ዋጋ አስከፋይና ግጭት ጠማቂ አካሄዶች በጭራሽ እንዲደገሙ አይፈቅድም።
"ፍትሕና ምሕረትም በየሚዛናቸው እንዲጓዙ መንግሥት ይፈልጋል" ያለው መግለጫው፣ በሂደቱ የተጎዱ ወገኖች እንደሚኖሩ በማመን የእነዚህ ተጎጂ ዜጎች ቁስል በሽግግር ፍትሕ የሚካስ መሆኑንም አስታውቋል።
"እነዚህ ተጎጂ ዜጎች ሕመማቸው ለኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ ሸክማቸውን መንግሥትና ሕዝብ በጋራ እንሸከምላቸዋለን"፣ ከእሥር የተፈቱ ወገኖችም ጭምር የተጎጂዎችን ሸክም የመሸከም ዕዳ አለባቸው" ሲልም ገልጿል።