አቶ ስብሃት “አሁን የቀብር ሥነ-ስርዓታችንን ነው በማስፈጸም ላይ ያላችሁት” ማለታቸውን ሌ/ጄኔራል ባጫ ገለጹ
የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ በመከላከያ ሰራዊት በቁጥጥር ስር መዋላቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴር ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል ተስፋየ አያሌውን ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ አቶ ስብሃት ነጋ እና ሌሎች የሕወሓት አመራሮች መያዛቸውን በገለጹበት ጊዜ ግለሰቦቹ የተያዙት በሰርጥ ውስጥ ተደብቀው ከነበረበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
አቶ ስብሃት በመከላከያ ሰራዊትና በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስልና ፎቶ ሲስቁ ታይተዋል፡፡ በርካቶችም አቶ ስብሃት ምን አሉ በሚል ሲነጋገሩ ነበር፡፡ የሕግ ማስከበር ዘመቻውን በራያ ግንባር በኩል ሲመሩ የነበሩት ሌፍተናንት ጄኔራል ባጫ ደበሌ እንደገለጹት አቶ ስብሃት ከተያዙ በኋላ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አቶ ስብሃት በተያዙበት ሰዓት ለከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች ፣ “እኛ እኮ ከሞትን ቆይተናል“ የሚል አስተያየት እንደሰጡ ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
አቶ ስብሃት ከመያዛቸው አስቀድሞ “ቢያዙ ምን ይሉ ይሆን“ ብለው ጄነራሎቹ ይወያዩ እንደነበር የገለጹት ሌፍተናንት ጄነራል ባጫ “ግለሰቡ ቢያዙ ሕገ መንግስቱ ጥሩ ነው ፤ ሕገ መንግስቱ እንደዚህ ነው… ብለው ነው የሚያወሩት“ የሚል ግምት በጄኔራሎቹ ሀሳብ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አቶ ስብሃት ከተያዙ በኋላም ልክ እንደተገመተው ፣ አንደኛው ጄኔራል ሲያናግሯቸው “ሕገ መንግስቱ ጥሩ ነው፤ ተወያዩበት“ እያሉ ሲያወሩ እንደነበር የምዕራብ ዕዝ አዛዥ እንደገለጹላቸው ሌፍተናንት ጄነራል ባጫ ገልጸዋል፡፡
ሌ/ጄኔራል ባጫ ተጫዋች ያሉት የምዕራብ ዕዝ ሌላ ጄኔራል አቶ ስብሃትን “ስለ ሕገ መንግስቱ ተወውና አንተ እስኪ ምን ይሰማሃል“ ብሎ እንደጠየቋቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ስብሃት ሲመልሱ “እኔ የሚሰማኝ እኛ ከሞትን እኮ ቆይተናል“ የሚል ነው፡፡
“መቸ ነው የሞታችሁት“ የሚል ጥያቄ እንደተነሳላቸው ያስታወቁት ሌ/ጄነራል ባጫ “እኛ የሞትነውማ ኢህአዴግ የሚባለው የጠፋ ጊዜ ነው ፤ አሁን የምታደርጉት ምን እንደሆነ ልንገርህ? አሁን እያደረጋችሁ ያላችሁት የቀብር ሥነ ስነስርዓታችን እየፈጸማችሁ ነው“ ሲሉ መመለሳቸውን አንስተዋል፡፡