ህወሓት “ከመንግስት ጋር በሌሎች አካላት በኩል እየተወያየሁ ነው” ማለቱን መንግስት አስተባበለ
የሀገሪቱን ህብረብሄራዊነት ለሚያስጠብቅ ማንኛውም የሰላም አማራጭ በሩ ክፍት መሆኑን መንግስት አስታውቋል
ህወሓት በሌሎች አካላት በኩል ከመንግስት ጋር ስወያይ ነበር ማለቱ ይታወሳል
የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር ድርድርም ይሁን ንግግር አለመጀመሩን አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት፤ “የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም እና ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለሚያስጠብቅ የትኛውም ለሰላም አማራጭ በራችን ከፍት ነው”።
ሆኖም ግን “ከህወሃት ጋር ስለመደራደር እስካሁን ድረስ በመንግስት በኩል የተወሰደ አቋም የለም” ሲሉ ተናግረዋል።
የህወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካዔል (ዶ/ር) በሌሎች አካላት በኩል ከመንግስት ጋር ሲወያዩ እንደነበር ከሰሞኑ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
“በውይይቶቹ ውጤት ተገኝቷል ያሉት” ዶ/ር ደብረ ጽዮን፤ “አሁንም ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሔዎችን እንፈልጋለን” ብለው ነበር።
በዚህ ዙሪያ መልስ የሰጡት ዶ/ር ለገሰ፤ “ህወሃት ማንኛውንም አይነት የፖለቲካ መሳሪያ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም፤ ህብረተሰቡ ውስጥ ክፍፍል መኖሩን ካረጋገጠ አለመተማመን እንዲፈጠር እንዲህ አይነት ነገር ይጠቀማል” ብለዋል።
“ህዝቡ ዘንድም መንግስት እኛን ዋሽቶ ከጀርባችን ከእነሱ ጋር እየተነጋገረ ነው እንዲባል ስለሚፈልጉ ነው እንደዛ የሚያደርጉት” ብለዋል።
“መንግስት እስካሁን ከህወሓት ጋር የጀመረው ንግግርም ሆን ድርድር የለም” ሲሉም ተናግረዋል።
ከሰሜን ኢትዮጵያ ከለው ጦርነት ጋር በተያያዘም ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤ መንግስተ ወደ ትግራይ ክልል አልገባም ብሎ ጦርነቱን ማቆምን አስታውሰዋል።
ነገር ግን “በህወሓት በኩል ትንኮሳዎች አሉ” ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ “ትንኮሳዎች በሚደረጉባቸው አካባቢዎች ላይ ግን እርምጃ እየተወሰደ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በአፋር ክልል ላይ ዳግም በከፈተው ጥቃት ከ220 ሺህ በላይ ዜጎች ማፈናቀሉን የክልሉ መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል።