መንግስት፤ አምነስቲና ሂዩማን ራይትስ ዋች በሀገር ውስጥ የወሰን ጉዳይ ላይ መግባት `አይችሉም` አለ
አምነስቲና ሂዩማን ራይትስ ዋች በወልቃይት ላይ ትኩረቱን ያደረገውን ሪፖርት ይዘት በጥንቃቄ እንደሚመረምር ገለፀ
ድርጅቶቹ አንድን ወገን ከተጠያቂነት ለማዳን ጥረዋል ተብሏል
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች በሀገር ውስጥ ባሉ የወሰን ጉዳዮች ውስጥ መሳተፍ እንደማይችሉ የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለቱ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባወጡት መግለጫ ላይ ማምሻውን ምላሽ ሰጥቷል።
ድርጅቶቹ በወልቃይት የዘር ማጽዳት፣ የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎች ተፈጽመዋል የሚል ሪፖርት አውጥተው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት ድርጅቶቹ በወልቃይት ላይ ትኩረት አድርገው ያወጡትን ሪፖርት ይዘት በሚገባ እንደሚመረምረው ገልጿል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሰብዓዊ ሕግን የጣሱትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ያስታወቀው መንግስት ድርጅቶቹ ተጠያቂነትን ለአንድ ወገን ብቻ ሰጥተዋል ብሏል። ተጠያቂነትን ለአንድ ወገን ብቻ ማድረግ ፍትህን ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት አጋዥ አለመሆኑንም ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተመድ ሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙትን የመብት ጥሰቶች ከመረመሩ በኋላ መንግስት የጋራ የሚኒስትሮች ታስክ ማቋቋሙ ተገልጿል። ታስክ ፎርሱም ዛሬ ሁለተኛ ስብሰባውን በማድረግ አቅጣጫ ማስቀመጡ ተገልጿል።
በሀገር ውስጥ ወሰን ጉዳይ የሚመለከታቸው ሕገ መንግስታዊ አካላት እንዳሉ የጠቀሰው የመንግስት መግለጫ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ መግባት እንደሌለባቸው ጠቅሷል።
ድርጅቶቹ ይፋ ያደረጉት ሪፖርት ለፖለቲካዊ ዓላማ ሊውል እንደሚችል ማወቅ አለባቸው ያለው መንግስት፤ ሌሎች ኃይሎችን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል ብሏል።
የመንግስት መርማሪ አካል ምንም እንኳን ሪፖርቱ ደካማ ጎን ቢኖውና እና መከላከያና ሌሎች ኃይሎችን ያለጥፋታቸው ቢወነጅልም እንደሚመረምረው ገልጿል።