የህወሓት ታጣቂዎች በንፋስ መውጫ ከተማ በ9 ቀናት ውስጥ 71 ሴቶችን አስገድደው ደፍረዋል - አምነስቲ
ወንጀሎቹ የተፈጸሙት በህጻናት ፊት መሆኑንም ድርጅቱ ገልጿል
ሴቶቹ የተደረፈሩት የህወሓት ታጣቂዎች በከተማዋ በቆዩባቸው ዘጠኝ ቀናት ውስጥ ነው
የህወሓት ታጣቂዎች በንፋስ መውጫ ከተማ 71 ሴቶችን አስገድደው መድፈራቸው ተገለጸ፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም አምኒስቲ ኢንተርናሽናል የህወሓት ታጣቂዎች በወረራ በያዟቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ያደረሱትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስመልክቶ ያጠናቀረውን ሪፖርት አውጥቷል፡፡
“ህወሓት ወራሪ እንጂ ተጎጂ አይደለም”- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
ተቋሙ በሪፖርቱ እንደገለጸው የህወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ንፋስ መውጫ ከተማ ከነሀሴ 6 ቀን እስከ 15 ቀን 2013 ዓ.ም በከተማዋ በቆዩባቸው ዘጠኝ ቀናት ውስጥ የተለያ ጥቃቶችን ፈጽሟል፡፡
ታጣቂዎቹ ከፈጸሟቸው ወንጀሎች መካከል በቡድን ሴቶችን መድፈር፣ ንብረት ማውደም፣ መዝረፍ እና አጸያፊ ስድቦችን በንጹሃን ላይ መፈጸማቸውን ድርጅቱ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ስለተፈጸመባቸው የቡድን አስገድዶ መደፈር አስመልክቶ በአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው ሴቶች መካከል አንዷ ገበያነሽ የተባለች የከተማው ነዋሪ ናት፡፡
ምግብ በመሸጥ እንደምትተዳደር የገለጸችው የ30 ዓመቷ ገበያነሽ "የሆነብኝን መናገር ቀላል አይደለም። ለሶስት ሆነው ደፈሩኝ። የደፈሩኝ ልጆቼ እያለቀሱ ነው። ትልቁ ልጄ 10 ታናሹ ደሞ 9 ዓመቱ ነው። ሁለቱም ወታደሮቹ ሲደፍሩኝ እያዩ ያለቅሱ ነበር። ከደፈሩኝ በኃላ እየሰደቡኝ ሽሮና በርበሬ ወሰዱ። በጥፊ መቱኝ። በፊቴ መሳሪያቸውን እያቀባበሉ እንደሚገድሉኝ አስፈራሩኝ" ስትል ተናግራለች፡፡
ሌላኛዋ በህወሓት ታጣቂዎች በቡድን የተደፈረችው የ28 ዓመቷ ሀመልማል ስትሆን እንጀራ በመሸጥ ሕይወቷን የምትመራ የከተማው ነዋሪ ናት።
"የ10 ዓመትና የ2 ዓመት ልጆች አሉኝ። ወታደሮቹ ልጆቼን እንዳይገድሉብኝ ፈርቼ ነበር። ልጆቼን አትግደሉብኝ እኔን እንደፈለጋችሁ አድርጉ አልኳቸው። ትንሿ ተኝታ ነበር። ትልቋ ግን እያየች ደፈሩኝ። ምን እንዳየች ለመናገር አቅሙ የለኝም" ስትል በህወሃት ታጣቂዎቹ የደረሰባትን ተናግራለች፡፡
ታጣቂዎቹ የህክምና ተቋማትን ማውደማቸውን የገለጸው ይህ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋም በተለይም ተገደው የተደፈሩ ሴቶች ህክምና እንዳያገኙ መደረጉንም አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ቃለመጠይቅ ካደረጋቸው 16 ሴቶች መካከል 14ቱ በህወሓት ታጣቂዎች በቡድን መደፈራቸውን ተናግረዋል፡፡
በአፋር ክልል ህወሓት በፈጸመው ጥቃት 107 ህጻናትን ጨምሮ 240 ተፋናቃዮች መግደሉን የክልሉ መንግስት አስታወቀ
አምነስቲ አክሎም በንፋስ መውጫ ከተማ በአጠቃላይ 70 ሴቶች በታጣቂዎቹ መደፈራቸውን ከከተማው ሴቶች እና ህጻናት ጽህፈት ቤት መስማቱንም በሪፖርቱ አካቷል፡፡
የተቋሙ ዋና ጸሃፊ አግኔስ ካላማርድ በማጠቃለያ ሪፖርቱ ላይ በሰጡት አስተያየት “የህወሓት ታጣቂዎች በንፋስ መውጫ ከተማ የጦር ወንጀል መፈጸሙን ከተጎጂዎች ያገኘነው መረጃ ያስረዳል” ብለዋል፡፡
የቡድኑ ታጣቂዎች አሁንም በአማራ እና አፋር ክልሎች ጥቃቱን ቀጥለዋል ያሉት ዋና ጸሃፊው እየፈጸሟቸው ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲያቆሙ ጠይቀዋል፡፡