በትግራይ በ3 ሰራተኞቹ ላይ በተፈጸመው ግድያ እጅጉን ማዘኑን የድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ገለጸ
የአሜሪካ መንግስት በበኩሉ ድረጊቱ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል አውግዞታል
የኢትዮጵያ መንግስት ድርጊቱ የተፈጸመው በህወሐት ለመሆኑ ቅድመ መረጃ ደርሶኛል ብሏል
የድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ዋና ዳይሬክተር ማርታ ካናስ “በትላንትናው ዕለት ከትግራይ የተሰማው የድርጅታቸው ሰራተኞች ህልፈት እጅጉን አዝነናል” ብሏል፡፡
“ግንኙነት እስከነበረበት ወቅት ድረስ፤ የእርዳታ አስተባባርያችን ማርያ ሄርናንዴዝ፣ ረዳት አስተባባርያችን ዮሀንስ ሓለፎም ረዳ እንዲሁም ሼፌራችን ቴድሮስ ገ/ማርያም በትላንትናው ዕለት ከሰዓት እየተጓዙ ነበር፤ ነገር ግን ጠዋት ስናይ መኪናው ባዶ ነው፣ አስክሬናቸውም የተወሰነ ሜትር ርቀት ላይ አገኘነው” ሲሉም ነው ሀዘናቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ ማርታ ካናስ፡፡
ድርጊቱ በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ አሳዘኝና አስደንጋጭ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የተፈጸመው ግድያ እንደሚኮኑኑትና በቀጣይም የሆነውን ሁሉ ለማወቅ እና ለፍትህ ሳይሰለቹ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
“የማሪያ ፣ የዮሃንስ እና የቴድሮስ ሞት ለድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ( MSF- Médecins Sans Frontières ) አካል ለሆንን ሁላችንም ከባድ ጉዳት ነው”ም ብሏል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ማርታ ካናስ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ “ዓብይ ዓዲ” አካባቢ በ3 የሰብዓዊ ሰራተኞች ላይ በተፈጸመው ግድያ እጅጉን ማዘኑን የአሜሪካ መንግስት ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ባወጣው መግለጫ በሰብዓዊ ሠራተኞች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ተቀባይነት የሌላቸውና ሊቆሙ የሚገባቸው ናቸው ብሏል፡፡
ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድና ወንጀለኞች ወደ ህግ እንዲቀረቡ ሲልም ጥሪ አቅርበዋል የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤቱ በመግለጫው፡፡
የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ደህንነት የመጠበቅ፣ያለተገደበ የእርዳታ ስረጭት እንዲኖር የማድረግ ሙሉ ኃላፊነት የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን በማስታወስ ጭምር፡፡
አሁንም ቢሆን “በተፋላሚ ኃይሎች የሚደረገው ውግያ ማቆም” እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ለመርዳት እጅጉን እንደሚበጅ መግለጫው አመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮ/ል ጌትነት አዳነ የድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ሰራተኞች የተገደሉት በህወሐት ኃይሎች ነው ብለዋል፡፡
"የህወሃት ታጣቂ ቡድን ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን (MSF- Médecins Sans Frontières ) የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሰራተኞችን ከመኪና አስወርዶ እንደገደላቸው ቅድመ መረጃ ደርሶናል" ብለዋል ኮ/ል ጌትነት፡፡
ከሟቾቹ ውስጥ አንዷ ስፔናዊ ስትሆን ሁለቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው አክለውም "በየትኛውም መመዘኛ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎችን መግደል ተቀባይነት የሌለውና ሰላም ወዳድ ሁሉ ሊያወግዘው የሚገባ ጭካኔ ነው" ብሏል።
"መላው የሀገሪቱ ህዝቦችና የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ይህን የሽብር ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ከመከላከያ ጎን እንዲሰለፍና ድርጊቱን በተገቢው አጣርቶ እንዲያወግዝ እንጠይቃለን" ነው ያሉት።
ሰራዊቱ ጉዳዩን ለሚያጣራ አካል ደጋፍ በማድረግ በራሱም በጠንካራ ማስረጃ አስደግፎ እንደሚያቀርብም አስታውቋል፡፡