ህወሃት ከሌሎች የሽብር ቡድኖች ጋር “እያደረገ ያለውን መጥፎ” ጥምረት አጋሮች በጥንቃቄ እንዲያዩት መንግስት ጠየቀ
ከትናንት ጀምሮ 318 ተሽከርካሪዎች መቀሌ ገብተዋል ተብሏል
መንግስት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በግጭቱ ከአፋርና ከአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ከ300 ሺ በላይ ዜጎች በጋራ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል ብሏል
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት በቀጣናው ካሉ የሽብር ቡድኖች ጋር የሚያደርገውን “መጥፎ” ትብብር አጋሮች በጥንቃቄ እንዲመለከቱት የኢትዮጵያ መንግስት ጠየቀ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ፕሬስ ሴክሬተሪያት የውጭ ቋንቋዎች እና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ህወሓት አሁንም የሽብር ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና ጸጥታ ችግር እንደሆነም ቢለኔ ስዩም ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ዓለም አቀፍ አጋሮች፤ ህወሃት በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች ጋር ያለውን መጥፎ ትብብር በጥንቃቄ ሊመለከቱት እንደሚገባ የገለጹት ቢለኔ ስዩም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የተፈረጀውን ህወሃት የሚፈጽማቸውን “የሽብር” ድርጊቶች ሊያወግዝ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ህወሃት፤ በቅርቡ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጥቃት መፈጸሙን እና ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች “በከፍተኛ ደረጃ“ ሕዝብ ማሸበሩን፤ የግለሰቦችን ንብረት መዝረፉን፤ የሕክምና ተቋማትን ጨምሮ የመሰረተ ልማት አውታሮችን እያወደመ መቀጠሉን ቢለኔ ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው ቦታዎች “የመከላከያ ሠራዊት የሚገኝበትን ሥፍራ ጠቁሙ” በሚል ንጹሃንን እያንገላታ እና እየገደለ መሆኑንንም ተናግረዋል፡፡ ህወሃት ትናንትና በደብረ ታቦር ከተማ በተኮሳቸው ከባድ መሳሪያዎች ንጹሃንን መግደሉን አረጋግጠዋል፡፡
ቢለኔ ስዩም፤ መንግስት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም፤ ሕወሃት በፈጸማቸው ጥቃቶችም ከአፋርና ከአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ከ300 ሺ በላይ ዜጎች በጋራ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ከትናንትና ጀምሮም ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን የያዙ 318 ተሽከርካሪዎች መቀሌ መግባታቸውንም ቢልለኔ ስዩም አስታውቀዋል፡፡