መንግስት “የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ” እስርን እንዲያቆም ኢሰመኮ ጠየቀ
መንግስት እየወደሰ ያለው እርምጃ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ያለመ ነው ብሏል
መንግስት ጋዜጠኞችን “በስራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን” ከማሰር እንዲታቀብም ተቋሙ አሳስቧል
መንግስት “የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ” እስሩን እንዲያቆም ኢሰመኮ ጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰሞንኛ ጉዳዮች ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች እያካሄዱት ባለው “የሕግ በላይነትን ማስከበር” እርምጃ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ታስረዋል ብሏል፡፡
ይሄንን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተልኩት ነው ያለው ኢሰመኮ “የተወሰኑት ተጠርጣሪ ታሳሪዎች በቤተሰቦቻቸው የተጎበኙና በተለያየ የጊዜ መጠን ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፤ በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት ያለመቅረባቸውን፣ በቤተሰብ” አለመጎብኘታቸውን መመልከቱን ገልጿል።
ኢሰመኮ በተለይም በአማራ ክልል “በርካታ በርካታ ታሳሪዎች ከመደበኛ መኖሪያ አካባቢያቸውና ከመደበኛ እስር ቦታዎች ውጭ ጭምር በመታሰራቸው ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን እንኳን ለማወቅ” መቸገራቸውን ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ሊወስድ የሚችላቸውን እርምጃዎች ኢሰመኮ ቢገነዘብም “የዚህ አይነት የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢ አለመሆኑን” የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል።
“በተለይም የፌደራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከወንጀል ምርመራ በፊት ከማሰር፣ ጋዜጠኞችን በስራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀቡ ይገባል ብሏል ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ።
ኢሰመኮ በማናቸውም አይነት ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ቤተሰቦቻቸው ወዲያውኑ እንዲያውቁ እንዲደረግና ወደ ፍርድ ቤትም ሊቀርቡ ይገባል” ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት እርምጃው ትክክል እና የህግ የበላይትን የማስከበር አላማ እንዳለው ይገልጻል፡፡
በአማራ ክልል ህገ-ወጥነት እንዲስፋፋ ያደረጉ አካላትን የለየ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ የገለጸው የክልሉ መንግስት ተጠርጣሪዎችን ከህግ ውጭ እያያዘ ነው የሚል ትችት ከተለያዩ አካላት እየተሰነዘረበት ነው፡፡