አቶ ብርሃኑ አዴሎ ከዚህ ቀደም ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትርና ነበሩ
አቶ ብርሃኑ አዴሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር በመሆን ተሸሙ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አዲስ ኮሚሽነር ሹመት በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
በዙሀም መሰረት አቶ ብርሃኑ አዴሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር በመሆን ተሹመዋል።
ለሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮምሽነር በመሆን የተመረጡት አቶ ብርሃኑ በጉባዔው ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ መፈጸማቸውንም ከምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሰረት አቶ ብርሃኑ አዴሎ የቀድሞውን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለን (ዶ/ር) በመተካት የኢመኮ ዋና ኮሚሽነር ሆነዋል።
አቶ ብርሃኑ አዴሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን፤ የ1997 ምርጫ ተከትሎ ነው የምር ቤቱ አባል የነበሩት።
አቶ ብርሃኑ አዴሎ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አንዱ ነው።
እንዲሁም በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ።
ከመንግስታዊ የሥራ ኃላፊ ከተነሱ በኋላ ላለፉት 10 ዓመታት በጥብቅና እና በህግ ማማከር ስራ ላይ መሰማራታቸውን በምክር ቤቱ የቀረበው የስራ ልምዳቸው ያመለክታል።
ላለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን በዋና ኮሚሽነርነት ሲመሩ የነበሩት ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር )የሥራ ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸውን ተከትሎ መሰናበታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ራኬብ መለሰ ጊዜያዊ ኮሚሽነር ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል።