በወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ ሰዎች ለዋስትናና ለምርመራ የተያዙ ገንዘቦችና ንብረቶች ለምን በጊዜው አይመለሱም?
የክስ መዝገብ እልባት አለማግኘት ወይም መዘግየት ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ- ፍትህ ሚኒስቴር
በታሰሩበት ወቅት የተያዙ ንብረቶችና ገንዘብ ሳይመለስላቸው ዓመታት ማለፋቸውን ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ
እርስዎ ድንገት በሆነ ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውሉ ይችላሉ፡፡ የሚታሰሩት ድንገት አገር አማን ብለው ወደ ጉዳይዎ እየተጓዙ አልያም በቤትዎ ውስጥ እያሉ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የያዙ ፖሊሶች ቤትዎትን ሲፈትሹ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር ግንኙነት ያላቸው አልያም ያልተያያዙ ንብረቶች በፖሊስ ሊወሰዱ ይችላሉ።
በፖሊስ የተያዙት ከመኖሪያ ቤትዎ ውጪ ከሆነ ደግሞ ስልክዎ፣ ላፕቶፕ አልያም ሌሎች ንብረትዎ አብረው ሊያዙ ይችላሉ።
እርስዎ በተጠረጠሩበት ወንጀል ነጻ ተብለው አልያም ጥፋተኛ ተብለው ሊሆን ይችላል። እንዲሁም በውጪ መከራከር ይችላሉ ተብለው በዋስትና ሊለቀቁም ይችላሉ።
- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሀብትን የሚያስመልስ ዳይሬክቶሬት አደራጀ
- የኢትዮጵያ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው ተያዙ
አል ዐይን አማርኛ በዛሬው ትኩረቱ ለዋስትና ስለ ተከፈለ ገንዘብ አመላለስ፣ በኤግዚቢትነት ስለተያዙ ንብረቶች እና ተያያዥ ጉዳዮችን ይዳስሳል።
ለደህንነቱ ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ግለሰብ እንዳለን “አገር አማን ብዬ በምኖርበት ቤት ፖሊሶች የፍርድ ቤት መፈተሸ ፈቃድ ይዘው መጥተው እኔን እና የተወሰኑ ንብረቶቼን ይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ” ይላሉ።
“ፖሊስ ምርመራውን እስከሚያጣራ ድረስ በእስር ቤት እንድቆይ ፍድር ቤትን በጠየቀው መሰረት ለወራት ታሰርኩ” የሚሉት እኝህ ግለሰብ “ፖሊስ ምርመራውን ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ በሰጠው ጊዜ ቀጠሮ ውስጥ ባለማጠናቀቁ እና እኔም በመጠየቄ ምክንያት ፍርድ ቤቱ ዋስትናዬን ጠብቆልኝ ከእስር ተከቀኩ” ሲሉ ነግረውናል።
ይሁንና “ይህ ምርመራም ሳይጠናቀቅ፣ የተጠረጠርኩበት ወንጀልም እልባት ሳይሰጠው፣ስታሰር የተያዘብኝ የእጅ ስልክ፣ላፕቶፕ እና ለዋስትና ያስያዝኩትም ገንዘብ ሳይመለስልኝ ዓመታት አልፈዋል” ሲሉ ነግረውናል።
“ንብረቴ እንዲመለስልኝ እና የተጠረጠርኩበት ወንጀልም መዝገቡ እልባት ተሰጥቶት የዋስትና ገንዘቤም እንዲመለስልኝ በተደጋጋሚ ብጠይቅም ከማመላለስ ውጪ መፍትሄ አላገኘውም” ሲሉ አስተያየት ሰጪ ጠቁመዋል።
ከስድስት ወር በፊት በወንጀል ተጠርጥረሀል በሚል በፖሊስ ታስረው በእስር ማሳለፋቸውን የነገሩን ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉን “ድንገት ከምዝናናበት ቦታ በወንጀል ተጠርጥረሃል” በሚል በፖሊስ መታሰራቸውን፣ ከዚያም ፍርድ ቤት ቢቀርቡም ምርመራው ተጠናቆ አቃቢ ህግ ክስ ሊመሰርትባቸው አለመቻሉን ተከትሎ “ፍርድ ቤቱ በነጻ አሰናብቶኝ ከእስር ብለቀቅም ስታሰር አብረውኝ የተያዙ ስልክ እና ሌሎች ንብረቶቼን ማግኘት አልቻልኩም” ብለዋል።
“ንብረቶቼ እንዲመለሱልኝ በተደጋጋሚ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ብመላለስም የተጠረጠርክበት የክስ መዝገብ ውሳኔ አልተሰጠበትም፣ አቃቢ ህግ በመዝገቡ ላይ ውሳኔ ካሰጠ በኋላ ንብረትህ ይመለስልሃል እባላለሁ” ሱሉም ጠቁመዋል።
ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ ፖለቲካ፣ ጋዜጠኝነት እና ተያያዥ ሙያ ውስጥ ላሉ ተጠርጣሪዎች ጥብቅና በመቆም ይታወቃሉ። አል ዐይን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የእሳቸውን ሙያዊ አስተያየት ጠይቋል።
ጠበቃ ሔኖክ እንዳሉን ብዙ የሚያውቋቸው እና ደንበኞቻቸው በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ሲታሰሩ እና ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች ጋር ግንኙነት አሏቸው በሚል ብዙ ንብረቶቻቸው በፖሊስ እንደሚያዙባቸው ተናግረዋል።
አቃቢ ህግ መዝገቦች ላይ በፍጥነት ውሳኔ ያለማሰጠት፣ የምርመራ መዝገቦች ከፖሊስ ተጠናቀው ለአቃቢ ህግ ቢላክም በቶሎ ክስ አለመመስረት፣ የክስ መዝገቦችን አለመከታተል እና ሌሎች ችግሮች እንደሚታዩም ገልጸዋል።
በዚህ ምክንያት ተጠርጣሪዎች ለብዙ ችግሮች እንደሚዳረጉ የሚናገሩት ጠበቃ ሔኖክ ህጉ የሚለው አንድ ግለሰብ ከተጠረጠረበት ወንጀል ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ንብረቶች እንዲመለሱ፣ የተከሰሱባቸው መዝገቦች እልባት ከተሰጠ በኋላ ኢግዚቢቶች ወይም በእስር ወቅት የተያዙ ንብረቶች በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እና ትዕዛዝ መሰረት እንዲፈጸም ይላልም ብለዋል።
ብዙ ሰዎች ደንበኞቻቸው ከተከሰሱባቸው ክሶች በነጻ ወይም አያስከስስም ተብለው አልያም በዋስ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና ውሳኔ ከእስር ሲፈቱ ንብረቶቻቸው እንደሚያዙባቸው እና መመላለስ ሰልችቷቸው ንብረቶቻቸውን እንደሚያጡም አክለዋል።
ለአብነትም የእጅ ስልክ፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ ገንዘብ፣ የባንክ ሂሳብ ማዘጋት እና ሌሎችም ንብረቶች እንደማይመለሱላቸው ጠበቃ ሔኖክ ጠቁመዋል።
ተጠርጣሪዎች በዋስ በሚመለከተው የህግ አካል ከእስር እንዲፈቱ ከተደረገ በኋላ አቃቢ ህግ ለመዝገቡ እልባት ሳያሰጥ ሲቀር እና መዝገቡ በእንጥልጥል ላይ እንዲቆይ ሲደረግ በእግዚቢትነት የተያዙ ንብረቶች ለዋስ የተከፈለ ገንዘብ ለረጅም ዓመታት በፖሊስ እጅ እንደሚቆዩም ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለም በተለይም በተለያዩ መስኮች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ግለሰቦች ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የሚውሉ ግለሰቦች ከተጠረጠሩባቸው ጉዳዮች ውጪ የሆኑ ንብረቶቻቸውን አለመመለስ፣ ማንገላታት እና ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረግ በስፋት እንደሚታዩም ጠበቃ ሔኖክ ነግረውናል።
በፍትህ ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙንኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አወል ሱልጣን ለአል ዐይን እንዳሉት መሰል አቤቱታዎች ለተቋማቸው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
በዋስትና የተያዘ ገንዘብ ተጠርጣሪዎች በተከሰሱባቸው መዝገቦች ጥፋተኛም ተባሉ ነጻ የግድ ገንዘቡ ተመላሽ ይሆናል የሚሉት ዳይሬክተሩ የክስ መዝገብ እልባት አለማግኘት ወይም መዘግየት ከዚህ ጋር ተያይዞም ንብረቶች ለባለጉዳዮች አለመመለስ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
ይሁንና የዋስትና ገንዘባችን አልተለቀቀም፣ መዝገባችን እልባት አላገኘም፣ ከተከሰስንበት ጉዳይ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ንብረቶቻችን ታግደዋል እና ሌሎች መሰል የአገልግሎት ቅሬታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ስለሚታመን የቅሬታ ማቅረቢያ ወይም ይግባኝ ማለቻ ስርዓት መዘርጋቱንም አቶ አወል አክለዋል።
በመሆኑም በአገልግሎቱ ቅሬታ የተሰማቸው በየኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ግለሰቦች ወይም ተቃማት በአቅራቢያቸው ባሉ የፍትህ ተቋማት ቀርበው ቢያመለክቱ ጉዳያቸው እልባት ያገኛልም ብለዋል።