ከግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት በኋላ የኢንጂነር ስመኘው ቤተሰብ ምን አለ?
ለአበርክቷቸው ዘወትር ሲያመሰግኗቸው የሚደመጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ኢንጂነር ስመኘውን እንደ ብሄራዊ ጀግና ይጠቅሷቸዋል
“ሚኒስትሩ የጀግና ልጆች ናችሁ አይዟችሁ ብለውናል”- በዕምነት ስመኘው በቀለ
“ሚኒስትሩ የጀግና ልጆች ናችሁ አይዟችሁ ብለውናል”- በዕምነት ስመኘው በቀለ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በተያዘለት ዕቅድ መሰረት በመፈጸሙ ከፍ ያለ ደስታ እንደተሰማው የቀድሞው የግድቡ የግንባታ ፕሮጄክት ዋና ስራ አስኪያጅ የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ልጅ ተናገረ፡፡
የሙሌቱን መጠናቀቅ ዜና ከአያቱ መስማቱን ለአል ዐይን አማርኛ የተናገረው በዕምነት ስመኘው በቀለ መላ የቤተሰቡ አባላት በተሰማው ብስራት መደሰታቸውን ገልጿል፡፡
ቤተሰቡ የተሰማውን ደስታ ለማጋራት ወዲያውኑ ለውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ለዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ስልክ መደወሉን የተናገረም ሲሆን ሚኒስትሩ “አይዟችሁ የጀግና ልጆች ናችሁ” እንዳሉዋቸውም ነው የገለጸው፡፡
በዕምነት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዌር ምህንድስና የ2ኛ ዓመት ተማሪ ነው፡፡
ኢንጂነር ስመኘው ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ እየገነባቸው ያለውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነት የመሩ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡
ህይወታቸው እስካለፈበት እስከ ሃምሌ 19 ቀን 2010 ዓ/ም ድረስም ግንባታውን በስራ አስኪያጅነት መርተዋል፡፡
ኢንጂነሩ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅነታቸው አስቀድሞም በግልገል ጊቤ ቁጥር 2 የኃይል ማመንጫ ግድብ የግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነት አገልግለዋል፡፡
ለአበርክቷቸው ዘወትር ሲያመሰግኗቸው የሚደመጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደ ብሄራዊ ጀግና ሲጠቅሷቸው መመልከትም የተለመደ ነው፡፡
የኢንጂነሩ 2ኛ የሙት ዓመት ሊሞላ የቀናት ዕድሜ ብቻ ይቀረዋል፡፡