ያለፈ ትርክትንና ዘርን መሠረት ያደረጉ ክርክሮችን የሚከለክል ህግ እንዲወጣ ተጠየቀ
“በኦሮሚያ በተለይም በምዕራብ አርሲ ገጠር ወረዳዎች የደረሰውን ጉዳት ለመከላከል ሲደረግ የነበረው ጥረት ደካማ ነው” ያለው የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጉዳቱን የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል
የጸጥታና የፖሊስ ተቋማት አደረጃጀት ሪፎርም እንዲደረግም ምክረ ሃሳብ ቀርቧል
“ወደፊት የሚደረጉ የፖለቲካ ክርክሮችም ሆኑ ውይይቶች ያለፈ ትርክትንና ዘርን መሠረት ማድረጋቸውን የሚከለክል ህግ እንዲወጣ” እንባ ጠባቂ ተቋም ጠየቀ
በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ አርሲ ገጠር ወረዳዎች የደረሰውን ጉዳት ለመከላከል ሲደረግ የነበረው ጥረት ደካማ ነው ያለው የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በጸጥታና ፖሊስ ተቋማት የአደረጃጀት ለውጥ እንዲደረግ ምክረ ሃሳብ አቀረበ፡፡
ተቋሙ ቀደም ሲል በተጠቀሱት የክልሉ አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ አደረግሁ ባለው ስምሪት “በዜጎች ላይ የደረሰው ግድያ እጅግ አሰቃቂ እና ከአንድ ሰብአዊ ፍጡር ይደረጋል ተብሎ የማይታመን ወንጀል” የተፈጸመ መሆኑን ለመገንዘብ ስለመቻሉ ገልጿል፡ወንጀል” የተፈጸመ መሆኑን ለመገንዘብ ስለመቻሉ ገልጿል፡፡
ጥቃቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ብሄርን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሃይማኖትን በትላልቅ ከተሞች ደግሞ የመንግስት ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የተለዩ ዜጎች ላይ አነጣጥሮ መፈጸሙን የገለጸም ሲሆን የከፋ ጥፋትና ጉዳት ሳይደርስ ጥቃቱን መከላከል የሚቻልበት ሁኔታ ቢኖርም የጸጥታ ሀይሉን በመምራትና የአካባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበር ለመከላከል ሲደረግ የነበረው ጥረት ደካማ እንደነበር ለማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል፡፡
“አንዳድ የፖለቲካ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ተባባሪ መሆናቸውን ድርጊቱ በሚፈጸምበት ወቅት ፊት ለፊት ሰው እየሞተና ንብረት እየወደመ በነበረበት ሁኔታ ከፖሊስና ከመከላከያ በኩል ትዕዛዝ ከበላይ የመጠበቅ ሁኔታ እንደነበረ ለመገንዘብ ተችሏል”ም ነው ተቋሙ ያለው፡፡
በመሆኑም “የጸጥታ መዋቅሩ በተለይ ፖሊስ አሁን ያለውን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጥ ተከትሎ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ በሚያስችለው ቁመና እና አመለካከት እንደገና ሊደራጅ ይገባል” ሲልም አሳስቧል፡፡
“የፖሊስ አደረጃጀት በየደረጃው ባሉ ሲቪል የመንግስት መዋቅር የሚመሩ ሆነው የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ ስምሪትና ፖሊሲያዊ (Operational) ተልእኮው በተማከለ አደረጃጀት (Centralized) ለፌደራል ፖሊስ ቀጥታ ተጠሪ ሆነው የሚመሩበት ሁኔታ ቢፈጠር” ሲል ነው ምክረ ሃሳብ ያቀረበው፡፡
እንባ ጠባቂ ተቋሙ ክልሎች ሊኖራቸው ስለሚገባው የፖሊስ ሀይል አደረጃጀት የህግ ወሰን ይበጅለት ያለም ሲሆን በክልሎች ያለው ልዩ ሀይል የፌደራል ፖሊስ አካል ሊሆን በሚችልበት ጉዳይ ላይ መንግስት ምክክር እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
በግድያ እና ንብረት ማውደም ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን በቅንጅት ለህግ የማቅረብ ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ማረጋገጥ እንደቻለም ነው የገለጸው፡፡
መንግስት በቀጣይ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራውን አጠናክሮ ሊቀጥል እና ከአሰቃቂው የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋና ጭፍጨፋውን ተከትሎ ከተወሰዱት እርምጃዎች ብዙ ሊማር እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
ወደፊት የሚደረጉ የፖለቲካ ክርክሮችም ሆኑ ውይይቶች ያለፈ ትርክትንና ዘርን መሠረት ማድረጋቸውን የሚከለክል ህግ እንዲዘጋጅ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
“በዚህ ረገድ …አማራውን ከሌሎች ብሄሮች ጋር ለማጋጨት በመሳሪያነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት ከአጼ ሚኒልክ ጋር ተያይዘው የሚነሱት ትርክቶች ናቸው፡፡ ከሀጫሉ ግድያ በኋላም አንዳንድ የኢትዮጵያን መበተን የሚመኙ ሚዲያዎች በከፍተኛ ሁኔታ የፕሮፖጋንዳ ማዕከላቸው በማድረግ ምንም የማያውቀውን ዜጋ የጥቃት ሰለባ አድርገዋል፡፡ ባለፉት ስርአታትም ይሁን ወደፊት መሪዎች ጥፋት ሊያጠፉ ይችላሉ ስለዚህ ሊጠየቁ የሚገባቸው ራሳቸው መሪዎቹ እንጂ የወጡበት ብሄር ወይም ማህበረሰብ አይደለም” ሲልም ነው ህጉ እንዲወጣ ምክረ ሃሳቡን ያስቀመጠው፡፡
በሻሸመኔ በአካባቢው አስተዳደርና በህብረተሰቡ ትብብር ከ4 ሚሊዬን ብር የሚበልጥ ድጋፍ መደረጉንና የቤት ግንባታ ስራ መጀመሩን የገለጸው ተቋሙ በአርሲ ነገሌ እና ባቱ ከተማ ከሚደረጉ ድጋፎች ጋር በተያያዘ ችግሮች እንዳሉና ከክልልና ከፌደራል መንግስቱ እስካሁን የቀረበ ድጋፍ አለመኖሩን ለመመልከት ስለመቻሉም አስታውቋል።
በቀጣይም ትላልቅ የአገልግሎትና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ጥበቃ እንዲደረግ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ እንዲከበር እና መንግስት ለዜጎቹ መረጃ የመስጠት ሃላፊነቱን እንዲወጣ የጠየቀው ተቋሙ የመረጃና የሚዲያዎች ነጻነት ሊከበር እንደሚገባም አሳስቧል፡፡