ምክር ቤቱ የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀደቀ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት ለመሰየም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ላይ እየመከረ ነው
የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር በመላ ሀገሪቱ ለ6 ወራት ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ6 ወራት ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርምሮ አጸደቀ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 1ኛ አመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባው ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርምሮ በአንድ ድምጽ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።
ምክር ቤቱ በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት ለመሰየም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ለማጽደቅ እየተወያየ ነው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሔደው 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባው በሀገር ህልውና ሉአላዊነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ያወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/14 እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ይታወሳል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፤ አዋጁ የታወጀው በሀገር የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑና፤ ይህንንም አደጋ በመደበኛ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻሉ የጸጥታና የደህንነት ተቋማትንና ዜጎችን በማቀናጀት አደጋውን ለመቀልበስ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ ነው ብለዋል።
አዋጅ የሚያስፈጽመው “የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ” ሲሆን ይህም የሚመራው በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ስር እንደሚሆን ተገልጿል። ይህ ዕዝም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ (ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ) እንደሚሆን ተገልጿል።
ዕዙ የሀገሪቱን ሁሉንም የጸጥታ አካላት ማዘዝና ማንቀሳቀስ እንደሚችል ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈም የተቋቋመው ዕዝ ማንኛውንም መሳሪያ የታጠቀ አካልን የማዘዝና የማሰማራት ስልጣን እንደተሰጠው ጌዲዎን ጢሞቲዮስ ተናግረዋል።
የታጠቁ ኃይሎች ወደ ግዳጅ እንዲሰማሩ፤ መሰማራት የማይችሉ ከሆነ ደግሞ የታጠቁትን በአዋጁ መሰረት የመገናኛ ዘዴዎችንና የትራንስፖርት አገልግሎትን የመዝጋት ስልጣን የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ መንግስት በሽብር ከፈረጀው ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ብሎ የጠረጠረውን ማንኛውንም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝና ተጠያቂ ማድረግ እንደሚቻልም ነው የተገለጸው።
የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ፤ መንግስት በሽብር ከፈረጀው ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የጠረጠረውን ድርጅት ወይም ግለሰብ ቤትና ንብረት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መበርበር እንደሚችልም አዋጁ ስልጣን ሰጥቶታል።
ሚኒስቴሩ፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ሰው፤ ቀላለ ወንጀል ከሆነ እስከ ሶስት አመት የሚያስቀጣ ሲሆን ከባድ ወንጀል ከሆነ ደግሞ እስከ 10 አመት የሚፈጅ እስራት እንደሚያስቀጣ አስታውቋል።