የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋር ም/ቤት፤ ህወሓት የሰላም አማራጭ አለመሟጠጡን አውቆ ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲገባ ጠየቀ
ለሶስተኛ ጊዜ የተቀሰቀሰውን ውጊያ የጀመረው “ህወሓት ነው” ሲልም ም/ቤቱ ገልጿል
የውጪ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንዳይገቡና የሰላም መንገድን ብቻ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት፤ ህወሓት የሰላም አማራጭ እንዳልተሟጠጠ አውቆ ለወራት የነበረውን የተኩስ አቁም እርምጃ እንዲያከብር አሳሰበ።
የምክር ቤቱ ሰብሰቢ መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ህወሓት የተኩስ አቁም እርምጃውን በማክበር ወደ ሠላማዊ ወይይትና ድርድር እንዲገባ ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ለሶስተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን ውጊያ የቀሰቀሰው ህወሓት እንደሆነም የጋራ ምክር ቤቱ ገልጿል።
የህወሓት ኃይሎች ለትግራይ ሕዝብ ሠብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ተብሎ የተከማቸውን ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነደጅ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም መዝረፋቸው ከሰሞኑ በዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ሲገለጽ ነበር።
ምክር ቤቱም ከትግራይ ሕዝብ የተዘረፈው ነዳጅ በአስቸኳይ እንዲመልስ ጥያቄ አቅርቧል።
የውጪ ኃይሎች ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን እንዲሰበስቡና የሰላም መንገድን ብቻ አጥብቀው እንዲደግፉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ጠይቀዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ጦርነቱ በሚቆምበትና ሰላማዊ ውይይትና ድርድር በሚጀምርበት ሁኔታ ላይ በፍትሐዊነትና በገለልተኝነት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ነው ምክር ቤቱ የጠየቀው።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአየር ክልል ጥሶ በገባው የውጪ ሀገር አውሮፕላን ላይ እርምጃ መውሰዱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገልጸው ነበር።
ፊልድ ማርሻሉ አውሮፕላኑ አንቶሞቭ 26 እንደሚባልም መግለጻቸው ይታወሳል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ አየር ኃይል የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሶ የገባውን አውሮፕላን መቶ መጣሉን እንደሚደግፍ ገልጿል።
ምክር ቤቱ አሁንም የኢትዮጵያ አየር ኃይል መሰል ጥንቃቄና ጀግንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርግ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጿል።
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፤ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊያን ጦርነትን ከሚያባብሱ መልዕክቶችና ተግባራት ተቆጥበውና የሰላም አማራጭ ብቸኛው መንገድ መሆኑን እንዲረዱም ነው የጋራ ምክር ቤቱ የጠየቀው።
ከዚህ በፊት በተካሄዱትና አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ በተቀሰቀሰዉ ጦርነት የሚያተረፍ አካል ባለመኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የጦርነትን አስከፊነት ተረድተዉ ጦርነቱ በሚቆምብት ሁኔታ ላይ የበኩላቸዉን ድርሻ እንዲወጡም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰብሳቢ ጥሪ አቅርበዋል።።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ለወራት ቆሞ የነበረውን ጦርነት መጀመሩን ባወጡት ባሳለፍነው ረቡዕ ነሃሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ህወሓት ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሰራዊትና እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃይሎች ትግራይ ደቡባዊ አቅጣጫ ባለው ግንባር በኩል ተኩስ መክፈታቸውን አስታውቋል።
የህወሓት መግለጫን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በዛሬው እለት ጠዋት 11 ሰዓት በተያየ አቅጣጫ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል።
የፌደራል መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው ህወሓት ጋር ያለውን ግጭት በድርድር ለመፍታት ማስታወቁ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚደረደር መግለጹ ይታወሳል። ህወሓትም በተመሳሳይ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር።