ህወሃት በቀጣይ ጦርነት ለማድረግ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ
መንግስት ከህወሃት ጋር ለመደራደር በም/ጠ/ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ ቡድን አቋቁሟል
ቡድኑ የኢትዮጵያ ሰራዊት የማያውቀው ተተኳስ ደብቆ እንደነበር ገልጿል
በመንግስት በሽብር የሚፈለገውና ትግራይን እያስተዳደረ ያለው ህወሃት ለቀጣይ ጦርነት ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ፡፡
የቡድኑ ታጣቂዎች አዛዥ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በክልሉ ለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን 90 ደቂቃዎችን የፈጀ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የቀድሞው የመከላከያ ከፍተኛ መኮንን እና የአሁኑ የህወሃት ታጣቂዎች አዛዥ አሁን የተዘጋጀው ጦር “የፈለግነውን ነገር መፈጸም የሚችል ነው” ሲሉም ነው ለመገናኛ ብዙሃኑ የገለጹት፡፡
“አሁን ጊዜ አግኝተን ሰርተንበታል” ያሉት ጀነራል ታደሰ ወረደ “ሁሉንም ዝግጅታችንን ጨርሰናል” ብለዋል፡፡ በቀጣይ የሚደረጉት ጦርነቶች ከዚህ በፊት ከነበሩት የገዘፉ እንደሚሆኑ ያነሱት ታደሰ “ከትግላችን መጨረሻ የሚያደርሱን ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ጦር ጋር “ይህን ያህል ሞተ ገደልን፤ ገለመሌ የሚባለው ውሸት ነው፤ እርግጠኛ መሆን ያለባችሁ አንድ ነገር ነው፤ዝግጅታችንን ጨርሰናል” ሲሉም ነው በመግለጫቸው የተናገሩት፡፡
ከተለያየ ወገን “ለምን አታጠቁም? ለምን አትጀምሩም?" የሚሉ ጥያቄዎችንና ጉትጎታዎች እንዳሉ ያነሱት የህወሃት አዛዡ “መቼ እንጀምር? እንዴትና የት? የሚለውን ወታደራዊ ስራ ነው” ም ብለዋል፡፡
ህወሃት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ከፍተኛ የተተኳሽ እጥረት እንደነበረበትና የኢትዮጵያ ሰራዊት በፈለገው ሰዓት ሲያጠቃው እንደነበር የገለጹት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ጎሬሮ በሚባልና የኢትዮጵያ ጦር በማያውቀው ስፍራ ተተኳሽ ቀብሮ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ህወሃት ተተኳሾቹን ካገኘ በኋላ ውስን ቦታዎች እንደሚይዝ እንጂ ብዙ ድል አስመዘግባለሁ ብሎ እንዳልነበረም ነው ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ የገለጹት፡፡
የህወሃት ታጣቂዎች ከተንቤን የወጡት ውስን ተራራዎቸን ለማስለቀቅ እንደነበር የገለጹት አዛዡ፤ የትግራይ ሕዝብ “ያለስንቅ የወጣውን የትግራይ ታጣቂ መቀለቡን፤ መሣሪያ መሸከሙንና የተቀበረ መሳሪያ መደበቁን አንስተዋል፡፡
የህወሃት ታጣቂዎች፤ የኢትዮጵያን ጦር ማስወጣትና መበተን ላይ ሲያተኩሩ “ሌላውን የመደምሰስ ስራ የሰራው ህዝቡ ነው” ያሉ ሲሆን “የኢትዮጵያን ጦር ያሸነፍነው በእልህ በተሞላው አመራራችንና በህዝቡ ነው” ብለዋል ሌ/ጄ ታደሰ፡፡
የኤርትራ ጦር ጥፋት እንደፈጸመና ይህንን ግን እንዳልጠበቁ ያነሱት አዛዡ ቀጣይ የማይቀሩ ጦርነቶች እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡
ህወሓት የትግራይ ህዝብ ብቸኛው ወካይ ሆኖ በድርድሩ እንዳይቀርብ የትግራይ ተቃዋሚ ፖርቲዎች ጠየቁ
አዛዡ መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ መንግስት፤ በሽብር ከፈረጀው ህወሃት ጋር ለመደራደር ከወሰነና ተደራዳሪዎችን ካሳወቀ በኋላ ነው፡፡
በመንግስት የተሰየመው ተደራዳሪ ቡድን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ሲሆን የፍትህ እና የደህንነት ኃላፊዎች ተካተውበታል፡፡
ገዥው ፓርቲ ከህወሃት ጋር ያለው ግጭት በሰላም እንዲፈታ ስምምነት ላይ መደረሱን የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዐቃቤ ሕግ የህወሃትን ታጣቂዎች የሚመሩትን ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደንና ጀነራል ገብረፃድቃን ገ/ትንሣኤን ጨምሮ በ 74 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱ አይዘነጋም፡፡