አቶ ልደቱ ከተከሰሱባቸው ሁሉም ወንጀሎች ነፃ ተባሉ
ፍርድ ቤቱ “ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም ብለሃል“ የሚለው ክስ አቶ ልደቱን ወንጀለኛ ሊያስብል አይችልም ብሏል
አቶ ልደቱ በሶስት ወንጀሎች ተጠርጥረው ክስ ተመስረቶባቸው ነበር
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው ከተከሰሱባቸው ሁሉም ወንጀሎች ነጻ መባላቸውን ጠበቃቸው ለአል ዐይን አስታውቀዋል፡፡
ከጠበቆቻቸው መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አብዱል ጀቢር እንደገለጹት አቶ ልደቱ በሶስት ወንጀሎች ተጠርጥረው ክስ ተመስረቶባቸው ነበር፡፡ እነዚህ ከሶችም የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተከሰተው ሁከት ጋር በተያያዘ ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ብጥብጥ ማነሳሳትና መደገፍ ፣ ሕገ ወጥ መሳሪያ መያዝ እና የሽግግር መንግሥት ይመስረት የሚል ሰንድ ማዘጋጀት የሚሉ ነበሩ፡፡
አቶ ልደቱ በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው ለኦሮሚያ ፖሊስ ተላልፈው መሰጠታቸው የሚታወስ ሲሆን ዋስትናቸው ተጠብቆ ከእስር ወጥተው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው ሲከታተሉ ነበር፡፡ አቶ ልደቱ በምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕገ ወጥ መሳሪያ በመያዝ ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸው ነጻ መባላቸውም የሚታወስ ሲሆን ፣ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምስራቅ ሸዋ ቋሚ ችሎት “ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለመናድና ለመለወጥ አቅደዋል” በሚል ተከሰው ነበር፡፡ አቶ ልደቱ የተከሰሱባቸው ሰነዶች ሻሞ ፣ የሽግግር መንግስት እና ለውጡ ከድጥ ወደ ማጡ የሚሉ ሲሆኑ ፣ አዲሱ “27 ሲደመር ሁለት“ የሚለው መጽሐፍና በኦኤም ኤን ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ የነበረው ውይይት በማስረጃነት ቀርበው ነበር፡፡
መጽሐፍ ሆኖ የወጣው “27 ሲደመር ሁለት“ ገና በረቂቅ ደረጃ የነበረና ለሕዝቡ ያልተሰራጨ ፣ ቢሰራጭም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ሕገ መንግስታዊ መብት እንደሆነና ይህ በ“ፍጹም ወንጀል ሊሆን አይችልም “ በሚል ፍርድ ቤቱ መወሰኑን ጠበቃው ገልጸዋል፡፡
“ከመስከረም 30 ቀን 2013 በኋላ መንግስት የለም ብለሃል“ የሚለውን ክስ በተመለከተም አቶ ልደቱ የተናገሩት የሚያስከስስ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ መግለጹን አቶ አብዱል ጀባር ሁሴን ተናግረዋል፡፡ የዚህ ምክንያትም በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት አንድ በሕዝብ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጣ መንግስት የሚያገለግለው ለአምስት ዓመት በመሆኑና መስከረም 30 ላይ ሥልጣን ላይ የነበረው መንግስት ጊዜ ስለሚያበቃ መንግስትም ራሱ ይህንን በማወቅ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ወስዶ ሕገ መንግስታዊ ትርጓሜ እንዲሰጥ ማድረጉንም ፍርድ ቤቱ መጥቀሱን ጠበቃው አስታውቀዋል፡፡ አቶ ልደቱ ያደረጉት ንግግር ሕገ መንግስቱ ያስቀመጠው ስለሆነ "ወንጀል ሊሆን አይችልም" በሚል ፣ አቃቤ ሕግ አቶ ልደቱ ወንጀል ስለመፈጸማቸው ማስረዳት አልቻለም በማለት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምስራቅ ሸዋ ቋሚ ችሎት ከሁሉም ክሶች በነጻ አሰናብቷቸዋል፡፡