ጠቅላይ ፍ/ቤቱ አቶ ልደቱ እንዲፈቱ ለሚመለከታቸው አካላት ትዕዛዝ መስጠቱን የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል
የአቶ ልደቱ የ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲተገበር የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ወሰነ
በተደጋጋሚ ዋስትና ተፈቅዶላቸው በይግባኝ የታገደባቸው አቶ ልደቱ አያሌው አዳማ የሚገኘው የምስራቅ ሸዋ ፍርድ ቤት በ100 ሺህ ብር ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን ዉጭ ሆነው እንዲከታተሉ የፈቀደላቸው ዋስትና እንዲተገበር የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዛሬ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ለምስራቅ ሸዋ ፍርድ ቤት እና ለፖሊስ የጻፈውን ትዕዛዝ ይዘው ከአቶ ልደቱ ጠበቃዎች ጋር ወደ ፍርድ ቤቱ በመሔድ ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በዉሳኔው የአቶ ልደቱን የዋስትና ጥያቄ የተቀበለ ሲሆን 100 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን ዉጭ ሆነው እንዲከታተሉ ማዘዙን፡፡ የአቶ ልደቱ ጠበቆች ከልብ ህመማቸው ጋር ተያይዞ ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ባቀረቡት ጥያቄ ላይ አከራክሮ የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት ባሳለፈው ውሳኔ አቶ ልደቱ 100 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን ዉጭ ሆነው እንዲከታተሉ ማዘዙ ይታወሳል፡፡
ይሁንና የዋስትና ገንዘቡን በመክፈል አቶ ልደቱን ከእስር ለማስፈታት ጥረት ቢደረግም በድጋሚ አቃቤ ህግ ባቀረበው ይግባኝ ምክንያት ዋስትናቸው ታግዶ ቆይቷል፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አቶ ልደቱን ለማስፈታት ደብዳቤውን ለሚመለከታቸው አካላት በማድረስ ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አዳነ ትዕዛዙ የተላለፈላቸው አካላት ምላሽ ካልሰጡ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ እንደተነገራቸውም ከአል ዐይን ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
አቶ ልደቱ አያሌው የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በቢሾፍቱ ሁከት በማስነሳት እና ኋላ ላይ ደግሞ አንድ ህገ-ወጥ ሽጉጥ በቤታቸው በተደረገ በብርበራ ተገኝቷል በሚል አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው ክስ ነው በእስር ላይ የቆዩት፡፡