የብልጽግና ዓላማ ጠንካራ ፓርቲ በመሆን በእሱ የሚከወን ጠንካራ ሀገረ መንግስት መመስረት ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
የብልጽግን ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል
በፓርቲው ጉባዔ መክፈቻ ላይ የተለያዩ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተገኝተዋል
የብልጽግና ዓላማ ጠንካራ ፓርቲ በመሆን በእሱ የሚከወን ጠንካራ ሀገረ መንግስት መመስረት መሆኑን የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባዕ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል
ዛሬ የተጀመረው እና እስከ መጋት 4 2014 ዓ.ም የሚካሄደው የፓርቲው ጉባዔ ከፈተና ወደ ልዕልና በሚል መሪ ቃል ነው በመካሄድ የሚገኘው።
የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ብልጽግና ልዩ የሚያደርገው በመጤ ሳይሆን በሀገር በቀል እሳቤ የተመሰረተ ፓርቲ መሆኑ ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ “ብልጽግናን በኢትጵያ ምድር ለማረጋገጥ የሀሳብም የቁጥርም ብቃት ያለው ነው” ያሉት የፓርቲው ፕሬዝዳንት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ከዚህ በፊት ከነበሩ ፓርቲዎችና ድርጅቶች በቁጥርም፥ በአደረጃጀትም፥ በሀሳብም የተለየ ፓርቲ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፓርቲው በመላው ሀገሪቱ ከ11 ሚሊየን በላይ አባላት እንዳው በመግለፅ፤ ሁሉም ብሄሮች በሚገባቸው ልክ የተወከሉበት ፓርቲ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ብልጽግና ኢትዮጵያን መስሎ ኢትዮጵያን ን ለመወከል የመጣ ፓርቲ ነው ያሉ ሲሆን፤ የብልጽግና ዓላማ ጠንካራ ፓርቲ በመሆን በእሱ የሚከወን ጠንካራ ሀገረ መንግስት መመስረት ሲሉም አስታውቀዋል።
ሀገራዊ ምክከሩን በተመለከተም የብልጽግና ፓርቲ ፐሬዚዳንት ዐቢይ አህመድ፤ መንግስትም ሆነ ብልጽግና ፓርቲ ለሀገራዊ ምክከሩ ከፍተኛ ዝግጅትና ፍላጎት አላቻው ብለዋል።
ኢትዮጵያን የሚያፀና ሀሳብ ከሀገራዊ ምክክር መድረኩ እንደሚወለድ እንጠብቃለን ሲሉም ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ድርጅታዊ ጉባዔው እስከ መጋቢት 4 የሚዘልቅ ነው።
እስካሁን ሳይካሄድ በቆየው በዚህ ጉባዔ የተለያዩ ታላላቅ ሃገራዊ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እና ድርጅቱ የአመራር ሹም ሽር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በተለይ ኢትዮጵያውያንን ያማረሩት የጸጥታ እና ደህንነት፣ የኑሮ ውድነት እና ሌሎች አንኳር ሃገራዊ ጉዳዮች የጉባዔው ተቀዳሚ አጀንዳዎች ሆነው እንደሚመከርባቸውና የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡም ነው የሚጠበቀው።
በጉባዔው 1 ሺህ 600 የፓርቲው አባላት በድምፅ እንዲሁም እንዲሁም ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ከውጭ ሀገራት የተጋበዙ 400 እንግዶች ደግሞ ያለ ድምጽ እንደሚሳተፉ ድርጅቱ አስታውቋል።