“ድምፃችን ለግድባችን” በሚል መሪ ቃል ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን የሚያሰሙበት መርሀ-ግብር በሸራተን አዲስ ተካሂዷል
ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴው ግድብ ያላቸውን የአጋርነት ድምፅ እያሰሙ ነው
በሸራተን አዲስ ሆቴል “ድምፃችን ለግድባችን” በሚል መሪ ቃል በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴው ግድብ ያላቸውን አጋርነት እና ባለቤትነት የሚያሰሙበት መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡
ዝግጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ውኃ ሙሌትን በተመለከተ ደስታቸውን እንዲገልጹ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
በዝግጅቱ ላይ ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው እና የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ማስተባበሪያ ም/ቤት ጽ/ቤት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገብረስላሴ፣ አርቲስቶች እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር ህብረተሰቡ የመጨረሻው ሪቫን እስኪቆረጥ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ከ10 ሰዓት ጀምሮ ለግድቡ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በተደረገው ጥሪ መሰረት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የመኪና አሽከርካሪዎች የክላክስ ድምጽ እያሰሙ በማሽከርከር ላይ ናቸው፡፡
ሰንደቅ አላማም እያውለበለቡ ድምጻቸውን ያሰሙ አሽከርካሪዎችም ተስተውለዋል፡፡
በርካታ ሰዎችም በጩኸት እና በተለያዩ ድምጾች ድጋፋቸውን አሰምተዋል ፤ እያስሰሙም ነው፡፡
ወ/ሮ ሮማን ገብረስላሴ “ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ተነሥተን በራሳችን ወጪ ግድቡን 74 በመቶ በማድረስ የመጀመሪያውን ሙሌት ማከናወን ችለናል” በማለት ህብረተሰቡ ላሳየው ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።
ባለፉት ዓመታት ለግድቡ ግንባታ ከህብረተሰቡ ከ13 ቢሊዮን 680 ሚሊዮን በላይ ብር መሰብሰቡን እና ከዚህም 1 ቢሊዮን 6 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ገንዘብ በዳያስፖራው ተሳትፎ የተገኘ መሆኑንም ገልጸዋል።
የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የዉሃ ሙሌት ከሳምንት በፊት መከናወኑ ይታወቃል፡፡ ግድቡ በመጀመሪያው ዙር የዉሃ ሙሌት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ የያዘ ሲሆን ይሄም የመጀመሪያ ሁለት ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ የሚያስችል ነው፡፡ የተርባይኖቹ ተከላ በሚቀጥለው ዓመት ተከናውኖ የኃይል ማመንጨት ስራውም እንደሚጀምር የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ግድቡ ከዓባይ ወንዝ የማገኘውን ዉሃ ቀንሶብኝ ለችግር ይዳርገኛል የሚል አቋም ስታራምድ የቆየችው ግብፅ የዉሃ ሙሌቱ ከተከናወነ በኋላ የተለሳለሰ ዲፕሎማሲ የመጠቀም አዝማሚያ በማሳየት ላይ መሆኗ ተንጸባርቋል፡፡