”ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል በተካሔደው ሰልፍ ላይ “ህወሓት ትጥቅ እንዲፈታ” ተጠየቀ
ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ህወሓትን የሚያወግዝ የሚቃወም ሰልፍ ተካሄደ

ሰልፈኞቹ “በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም ጣልቃ ገብነት ይቁም፣ በድርድር ስም የህወሓት ዕድሜን ማራዘም ይብቃ” ሲሉም ጠይቀዋል
ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ለመቃወምና እና ህወሓትን ለማውገዝ አላማ ያደረገ ሰልፍ በዛሬው እለት ተካሂዷል።
”ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ!” በሚል መሪ ሀሳብ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተካሄደ ሰልፎች ላይ በርካታ ኢትዮያውያን ተሳትፈዋል።
በሰልፉ ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ምስጋና የቀረበ ሲሆን፤ የምእራባውያንን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም ህወሓን የሚያወግዝ መፈክሮች ተሰምተዋል።
በሰልፉ ላይ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ካሰሟቸው መፈክሮች መካልም “ህወሓት የችግሩ ምንጭ ነው፣ በድርድር ስም የህወሓት ዕድሜን ማራዘም ይብቃ፣ሁለት ሰራዊት በአንድ ሉዓላዊት አገር አይኖርም፣ ለዘላቂ ሠላም ህወሃት ትጥቅ ትፍታ እንዲሁም ህወሓት ቅጥረኛ ነው” የሚሉ ይገኙበታል።
ሰልፈኞቹ ምእራባውያንን በተቃወሙበት መልእክታቸውም፤ “በሉዓላዊነታችን አንደራደርም፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም ጣልቃ ገብነት ይቁም፣ በቤታችን ጣልቃ አትግቡ፣ ሉዓላዊነታችን አክብሩ” የሚሉ ይገኙበታል።
ሰልፈኞቹ አክለውም “የትግራይ ህዝብ ወገናችን ነው፤ ህወሓት ጠላታችን ነው፣ የትግራይ ብልጽግና የሚረጋገጠው ከእኛ ከወገኖቻቸው ጋር ነው” የሚሉ መልእክቶችንም አስተጋተዋል።
የሰልፉ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ እንደሆነ ታውቋል።