ቡልጋሪያ፣ ሰሜን ሜቄዶኒያ እና ሞንቴኔግሮ የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ሰርቢያ እንዳይሄዱ የአየር ክልላቸውን ዝግ ማድረጋቸው ሩሲያን አስቆጥቷል
ሶስቱ የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት፣የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስርጌ ላቭሮቭ ወደ ሰርቢያ እንዳይሄዱ የአየር ክልላቸውን መዝጋታቸው “ያልተጠበቀ” ነው ስትል ሩሲያ ተቃወመች፡፡
ሚኒስትሩ ሀገራቱ የአየር ክልላቸውን ለምን እንደዘጉ እስካሁን ማብራሪያ አላገኘንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአየር ክልሉ መዘጋት ወደ ስቢያ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ የተስተጓጎለባቸው ሚኒስትሩ የሰርቢያ አቻቸውን ወደ ሞስኮ እንዲመጣ መጋበዛቸውን ገልጸዋል፡፡
ቡልጋሪያ፣ ሰሜን ሜቄዶኒያ እና ሞንቴኔግሮ የሩሲያውን ከፍተኛ ዲፕሎማት ይዞ ወደ ሰርቢያ ቤልግሬድ ለማለፍ የሞከረውን አውሮፕላን የአየር ክልላቸውን በመዝጋት እንዳያልፍ አድርገዋል፡፡
ሩሲያ የሀገራቱን እርምጃ እንደ ጥላቻ እንቆጥረዋለሁ ብላለች፡፡
ላቭሮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርቢያን መጎብኘት በምዕራቡ ዓለም እንደ ስጋት ከታየ፣ በምዕራቡ ዓለም ነገሮች መጥፎ እየሆኑ መምጣታቸውን በግልጽ ያሳያል ብለዋል፡፡
ሩሲያ በላፈው የካቲት ወር በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ጥቃት የከፈተችው ምእራባውያን ዩክሬንን የኔቶ አባል ለማድግ እየተንቀሳቀሱ ነው፤ይህም ለደህንነቴ ያሰጋኛል በሚል ነበር፡፡
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ሩሲያ ዩክሬን ወደ ሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) እንዳትቀላቀል ማስጠንቀቂያ ስትሰጥ መቆየቷ ይታወሳል፡፡ በምእራባውያን የምትደገፈው ዩክሬን ግን ይህን ማስጠንቀቂያ አልተቀበለችውም ነበር፡፡
አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ሀገራት ሩሲያ ያዳክማል ብለው ያሰቡትን ሁሉ ማእቀብ ጥለዋል፤እየጣሉም ይገኛሉ፡፡
ሩሲያ ወዳጅ አይደሉም ያለቻቸው ምእራባውያን ሀገራት ነዳጇን በሩብል እንዲገዙ በማድረግ የተጣለባትን ማእቀብ ለመበቀል ሞክራለች፤ በዚህም የተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ፍላጎት ነጃጅ እየገዙ ነው፡፡
የአውሮፓ ህብረትም የነዳጅ ገዥ ኩባንያዎች በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማእቀብ በማይጻረር ምልኩ ነዳጅ በሩብል ምዛት ይችላሉ ማለቱም ይታወሳል፡፡
ጦርነቱ አሁንም በመካሄድ ላይ ሲሆን ሩሲያ የዶምባስ ግዛት ነጻ እስከሚወጣ ድረስ ይቀጥላል ብላለች፡፡