የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎች የአሜሪካ ባለስልጣናትም በማዕቀቡ ውስጥ ተካተዋል
የሩሲያ መንግስት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና በሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉን ሩሲያ ቱደይ (አርቲ) ዘግቧል።
ሞስኮ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አንቶኒ ብሊንከንና ሌሎች የአሜሪካ ባለስልጣናት ማዕቀብ እንዲጣልባቸው መወሰኗ አነጋጋሪ ሆኗል።
ከነዚህ በተጨማሪም የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን፣ የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጀን ሳኪ፣ የመከላከያ ሚኒስትሪ ሊዮይድ አውስቲንም ማዕቀብ ከተጣለባቸው ባለስልጣናት መካከል ይገኙበታል።
በተጨማሪም የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ተሩዶ ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ ማዕቀብ እንተጣለባቸውም ታውቋል።
ቀደም ሲል አሜሪካ በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው።
ዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በሞስኮ ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀቦችን መጣለቸው የሚታወስ ሲሆን ሩሲያ አሁን አጸፋውን መስጠት ጀምራለች።
ሩሲያ ከዚህ ቀደም የተጣሉባትን ማዕቀቦች አስመልክቶ በሰጠችው ምላሽ ምዕራባውያንን ልጎዳ እንደምትችል ማስጠንቀቋ ይታወሳል።