የአውሮፓ ህብረትና ሰባት ሀገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ ትጥቅ የማስፈታት፣ ተፈናቃዮችን የመመለስ እና የሽግግር ማስፈን ሂደቶች መፋጠን አለባቸው ብለዋል
የፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በጥቂት ወራት ውስጥ ዳግም በመገናኘት ለመነጋገር ተስማሙ።
የሁለት አመቱን የሰሜኑን ጦርነት ለማስቆም በጥቅምት ወር 2015 የተደረሰው ስምምነት አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቋል።
በአፍሪካ ህብረት በተካሄደው ግምገማ የፌደራል መንግስቱም ሆነ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለስምምነቱ የተሟላ ትግበራ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ቀናት በተነሱና በሌሎች ጉዳዮች ለመምከርም ከጥቂት ወራት በኋላ ዳግም ለመገናኘት ተስማምተዋል።
የግምገማውን መጠናቀቅ ተከትሎ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የብሪታንያ እና አሜሪካ ተልእኮዎች የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
ህብረቱ እና ሀገራቱ በአፍሪካ ህብረት የተደረገው የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት የመጀመርያ ግምገማ በበጎ እንደሚቀበሉት ነው ያስታወቁት።
የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ባለስልጣናት ልዩነቶችን በፖለቲካዊ ምክክር ለመፍታት የጀመሩትን ጥረት እንዲያጠናክሩ የጠየቀው መግለጫው ትኩረት ያሻቸዋል ያላቸውን ጉዳዮችም ዘርዝሯል።
በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ የማዋሃድ ስራው መፋጠን አለበት የሚለው ቀዳሚው ጉዳይ ነው።
በሁለት አመቱ ጦርነት የተጎዱ ሰዎችን መልሶ የማቋቋምና የተፈናቀሉ ሰዎችን በፈቃዳቸው ወደ ቀያቸው የመመለሱ ጉዳይም ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።
ተጎጂዎችን መሰረት ያደረገ የሽግግር ፍትህ እና ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል የሚለውም በጋራ መግለጫው የተጠቀሰ ነጥብ ነው።
የአውሮፓ ህብረትና የሰባቱ ሀገራት የጋራ መግለጫ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል በሚታዩ ተመሳሳይ ግጭቶች የሚሳተፉ አካላት በንግግር ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ቁርጠኛ እንዲሆኑም ጠይቋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈጻሚ ከሆነ ጀምሮ በትግራይ ክልል ሰላምና መረጋጋት መስፈኑንና የተቋረጡ አገልግሎቶችን በማስጀመር ረገድ ትልቅ ለውጥ መታየቱን የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሲናገሩ ይደመጣል።
ይሁን እንጂ በአማራ እና ኤርትራ ሃይሎች የተያዙ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ይዞታቸው (ትግራይ) እንዲመለሱና ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸው ይመለሱ የሚለው በስምምነቱ የተካተተ ነጥብ ተፈጻሚ አልሆነም የሚለው ጉዳይ የስምምነቱን ፈራሚዎች ሲያከራክር ቆይቷል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰብአዊ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ እየደረሰ አይደለም፤ በትግራይ ከ77ቱ የከፋ ድርቅ አንዣቧል ማለቱን ተከትሎም የፌደራል መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ትችት መሰንዘሩ ይታወሳል።
የፌደራሉ መንግስት የአማራ እና ትግራይ ክልሎችን በሚያዋስኑ አካባቢዎች መከላከያ በማስገባት የህዝበ ውሳኔ ለማድረግ መታቀዱን ገልጿል፤ ከሰብአዊ ድጋፍ ጋር ተያያዞ የሚቀርቡ ክሶችንም በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ግምገማም ሁለቱ ወገኖች ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸውና ዳግም ተገናኝተው ለመምከር መስማማታቸው ልዩነቶችን እንደሚያለዝብ ታምኗል።