የአፍሪካ ህብረት በፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ትኩረት ያሻቸዋል ያላቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
በጥቅምት ወር 2015 የተፈረመው ስምምነት አፈጻጸም የፌደራል፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የኢጋድ እና አሜሪካ ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተገመገመ ነው
በግምገማው የፖለቲካ ድርድር፣ የሽግግር ፍትህና የትጥቅ አፈታት ጉዳይ አስቸኳይ ትኩረት ይሻሉ ተብሏል
የሁለት አመቱን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም በአዲስ አበባ እየተገመገመ ነው።
በግምገማው ላይ የፌደራልና ትግራይ ክልል አመራሮች፣ የኢጋድ፣ የአፍሪካ ህብረትና የአሜሪካ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ከአንድ አመት ተኩል በፊት በህዳር ወር 2015 በደቡብ አፍሪካ ስምምነቱ እንዲደረስ ከፍተኛ ሚና የነበራቸውና በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታም በግምገማው ላይ ታድመዋል።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በናይሮቢ ሁለት ስብሰባዎችን ያደረገውና በመቀሌ የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተልና የሚቆጣጠር ቡድን ያቋቋመው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በስምምነቱ አፈጻጸም ዙሪያ የህብረቱን ግምገማ ያመላከተ ንግግር አድርገዋል።
ጦርነቱ ከስምምነቱ በኋላ ወዲያውኑ መቆሙ፣ መካከለኛና ከባድ መሳሪያዎች ትጥቅ የመፍታት እንዲሁም ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶችን የማስጀመሩ ጥረት ውጤታማ እንደነበር ሊቀመንበሩ አንስተዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ተቋቁመው ስራ መጀመራቸውንም የፕሪቶሪያው ስምምነት ያስገኛቸው ውጤቶች አድርገው ጠቅሰዋቸዋል።
ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የታዩ ለውጦች የሚካዱ ባይሆኑም አፋጣኝ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውንም ነው ሙሳ ፋቂ ማህማት ያብራሩት።
በፌደራል መንግስት እና በትግራይ አመራሮች መካከል የፖለቲካ ድርድር በፍጥነት አለመጀመሩን ያነሱት የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር፥ የሽግግር ፍትህን የማስፈን፣ የትጥቅ አፈታትና መልሶ ማዋሃዱ ሂደትም ፈጣን እርምጃ ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል ብለዋል።
ህብረቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሂደቱ ኢትዮጵያ መር እንዲሆን እንደሚፈልግና ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈጻሚ ከሆነ ጀምሮ በትግራይ ክልል ሰላምና መረጋጋት መስፈኑንና የተቋረጡ አገልግሎቶችን በማስጀመር ረገድ ትልቅ ለውጥ መታየቱን የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሲናገሩ ይደመጣል።
ይሁን እንጂ በአማራ እና ኤርትራ ሃይሎች የተያዙ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ይዞታቸው (ትግራይ) እንዲመለሱና ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸው ይመለሱ የሚለው በስምምነቱ የተካተተ ነጥብ ተፈጻሚ አልሆነም የሚለው ጉዳይ የስምምነቱን ፈራሚዎች ሲያወዛግብ ቆይቷል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰብአዊ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ እየደረሰ አይደለም፤ በትግራይ ከ77ቱ የከፋ ድርቅ ተከስቷል ማለቱን ተከትሎም የፌደራል መንግስት ጠንከር ያለ የተቃውሞ መግለጫ እንዲያወጣ ማድረጉ አይዘነጋም።
የፌደራሉ መንግስት የአማራ እና ትግራይ ክልሎችን በሚያዋስኑ አካባቢዎች መከላከያ በማስገባት የህዝበ ውሳኔ ለማድረግ መታቀዱን ገልጿል፤ ከሰብአዊ ድጋፍ ጋር ተያያዞ የሚቀርቡ ክሶችንም በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ሙሳ ፋቂ ማህማት በዛሬው የፕሪቶሪያ ስምምነት ግምገማ ላይ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስለሚነሱ ቅሬታዎች ሲናገሩ አልተደመጠም።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመርን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች በተሳተፉበት ግምገማ የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ዋነኛ ማነቆዎች ላይ በስፋት ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።