የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን 1 ቢሊዮን ዩሮ አፋጣኝ ድጋፍ አቀረበ
የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ቮን ዴር ሌየን “ድጋፉ የዩክሬንን ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያግዝ ነው” ብለዋል
የአውሮፓ ህብረት አሁን የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ቀደም ብሎ በዚህ ዓመት ከሰጠው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዩሮ ብድር ተጨማሪ መሆኑ ነው
የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን 1 ቢሊዮን ዩሮ አፋጣኝ ድጋፍ ማቅረቡ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ገርትሩድ ቮን ዴር ሌየን አስታወቁ፡፡
ሌየን በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ መልእክት “ድጋፉ የዩክሬንን ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያግዝ ነው” ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን የሚሰጠው እፎይታ እና የረጅም ጊዜ ድጋፍን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አክለዋል ፕሬዝዳንቷ፡፡
ድጋፉ የህብረቱ መሪዎች ቀደም ሲል በወርሃ ግንቦት፤ ለዩክሬን የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ በደረሱት ስምምነት መሰረት የሚከናወን ነው ተብሏል፡፡
በብሉምበርግ የታየው ረቂቅ ጽሁፍ እንዳመላከተው ከሆነ፤ የአውሮፓ ህብረት የዩክሬንን 2022 የፋይናንስ ክፍተትን ለመሸፈን ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት "ትልቅ" የእርዳታ አስተዋፅኦ ለማድረግ ይፈልጋል ።
ኮሚሽኑ የብድር መስመሩን ለመደገፍ በዚህ ክረምት መጀመሪያ ላይ በገበያ ላይ ገንዘብ ለማሰባሰብም ይፈልጋል።
የዩክሬን የፋይናንስ ሚኒስቴር በቅርቡ በሰጠው መግለጫ የፋይናንስ አማራጮች እያለቁ ነው ይህም ሀገሪቱ በውጫዊ እርዳታ ላይ የበለጠ ጥገኛ እንድትሆን አድርጓታል ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡
የዩክሬን ባለስልጣናት፤ ያላቸውን ሸክም ለማቃለል ከዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ጋር ያላቸውን ጥሩ ሚባል ግንኙነት ተጠቅመው እዳ አከፋፈል ላይ የእዳ መልሶ ማዋቀር እድልና አማራጭ ካለ የተቻላቸውን በማድረግ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አሁን የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ቀደም ብሎ በዚህ ዓመት ከሰጠው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዩሮ ብድር ተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡
የቡድን -7 አባል ሀገራት እስካሁን ለዩክሬን ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የፋይናንሺያል ድጋፍ ማድረጋቸውም የብሉምበርግ መረጃ ያመለክታል፡፡