የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ 10ኛውን ማዕቀብ ሊጥል ነው
ማዕቀቡ ሞስኮ ድሮን እና ሌሎች ወታደራዊ መሳሪያዎችን ለመስራት የምትጠቀምባቸውን ግብአቶች ከሌላ ሀገር እንዳታገኝ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተነግሯል
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንቶች በኬቭ ከዜለንስኪ ጋር መክረዋል
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የሚጥለውን 10ኛ ማዕቀብ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ተገለጸ።
ህብረቱ፥ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችበት አንደኛ አመት ላይ ነው ጠንከር ያለ ማዕቀብ እጥላለሁ ያለው።የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ላይን በኬቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ ማዕቀቡ በሩሲያ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።
ሞስኮ ድሮን እና ሌሎች ወታደራዊ መሳሪያዎችን ለመስራት የምትጠቀምባቸውን ግብአቶች ከሌላ ሀገር እንዳታገኝ ያደርጋል የተባለው ማዕቀብ ሌሎች በርካታ እገዳዎችንም ይጥላል ነው ያሉት።
ለሩሲያ ድሮኖችን ታቀርባለች በሚል የምትወቀሰውን ኢራንም በተዘዋዋሪ ይጎዳታል ተብሏል።
10ኛው ማዕቀብ ይጣል ዘንድ ግን 27ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ይሁንታ መስጠት ይኖርባቸዋል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
ቮን ደር ላይን ለዩክሬን አጋርነታቸን ለማሳየት ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል ጋር በመሆን ኬቭ ተገኝተዋል።የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለስልጣናቱ በጦርነት ውስጥ ያለችውን ዩክሬን መጎብኘታቸው የኬቭን የአውሮፓ ህብረት እና የኔቶ አባልነት ጥያቄ ድጋፍ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተነግሯል።
ህብረቱ እና ምክር ቤቱ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፎችን እንደሚያደርጉ በመግለጫቸው ቢያነሱም፥ የሀገሪቱ የአውሮፓ ህብረት አባልነት ጉዳይ ምን ደረጃ እንደደረሰ ከመናገር ተቆጥበዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በበኩላቸው፥ የአውሮፓ ህብረትን ለመቀላቀል በዚህ አመት ድርድር መጀመር አስበናል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሂደቱ ረጅም አመታትን እንደሚወስድ ገልጸው ሀገራቸውን ከህብረቱ አባል ሀገራት ጋር በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ኢነርጂ እና ጉምሩክ ለማስተሳሰር የተጀመሩት ጥረቶች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሀገራት ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለዩክሬን የ55 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል።
ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ብሪታንያን ጨምሮ በርካታ የህብረቱ አባል ሀገራትም ለኬቭ የጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ ላይ ናቸው።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽንም በአዲስ ማዕቀብ ሞስኮን ለማዳከም መዘጋጀቱን ተናግሯል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወደ ምስራቅ መስፋፋት ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ያስገባት ሩሲያ፥ የአውሮፓ ሀገራቱ የጦር መሳሪያ ድጋፍና የማዕቀብ ናዳ ጦርነቱን ከማርዘም ውጭ ፋይዳ የለውም ስትል ደጋግማ ገልጻለች።