አውሮፓ ህብረት የሩሲያ የዩክሬን ክልሎችን ወደ ግዛቷ መጠቅለል ዓለም አቀፍ ህግን ይጥሳል አለ
ሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን ወደ ግዛቷ በይፋ መጠቅለሏ በትናንትናው እለት አስታውቃለች
የህብረቱ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል “የዩክሬን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ለድርድር አይቀርብም” ብለ
አውሮፓ ህብረት፤ የሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን ወደ ግዛቷ መጠቅለል ዓለም አቀፍ ህግን እና የተመድ ቻርተርን መጣስ ነው አለ፡፡
የአውሮፓ ህብርት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል፤ የክሬምሊን ድረጊት ተቀባይነት የሌለው ህገ-ወጥ ድርጊት ነው ማለታቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
በህገ-ወጥ መንገድ የተደረገውን ህዝበ ውሳኔ 27 መሪዎች አውግዘውታልም ያሉት ቻርለስ ሚሼል፤ አውሮፓ ህብረት የይስሙላውን 'ሪፈረንደም' መቼም ቢሆን እውቅና እንደማይሰጠውም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የዩክሬን ግዛቶችን በህገ-ወጥ መንገድ ለመጠቅለል የተደረገው ጥረትም እውቅና አንሰጠም ሲሉ አክለዋል የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፡፡
የቻርለስ ሚሼልን ሃሳብ የሚጋሩት ሌላው የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮችና የደህንት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው አውሮፓ ህብረት፤ የሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን ወደ ግዛቷ መጠቅለል “ዓለም አቀፍ ህግን እና የተመድ ቻርተርን መጣስ ነው” ብለዋል፡፡
የትኛውም የይስሙላ ሪፈረንደም ትክክል ሊሆን አይችልም ያሉት ጆሴፕ ቦሬል የዩክሬን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ለድርድር እንደማይቀርብና ለዚህም የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን የሚሰጠው ድጋፍ የማያቋርጥ መሆኑ አረጋግጠዋል፡፡
ሩሲያ ህዝበ ውሳኔ የተካሄደባቸውን አራት የዩክሬን ክልሎችን ወደ ግዛቷ በይፋ መጠቅለሏ በትናንትናው እለት አስታውቃለች፡፡
የህዝበ ውሳኔው ደምጽ ውጤት እሮብ ይፋ የሆነ ሲሆን የአራቱ ግዛቶች 96 በመቶ ነዋሪዎቹ ወደ ሩሲያ መቀላቀል እንደሚፈልጉ መወሰናቸውን ተከትሎ በይፋ በዛሬው ዕለት የሩሲያ አንድ አካል መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ፑቲን በፊርማቸው እንዳጸደቁ ራሺያ ቱዳይ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ግዛት የነበሩት ሉሃንስ፣ኬርሰን፣ ዛፖሮዚየ እና ዶንቴስክ ክልል መሪዎች በተገኙበት የሩሲያ አካል መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከፊርማው ስነ ስርዓት በኋላ በሞስኮ ጎዳናዎች “ሩሲያ፣ ሩሲያ፣ ሩሲያ” የሚሉ መፈክሮች ሲሰሙ ነበርም ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አራቱን ግዛቶች የሩሲያ አካል መሆናቸውን የሚያረጋግጠውን ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ ባደረጉት ንግግር ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ “ ዩክሬን ጦርነቱ እንዲቆም ከፈለገች የጥላቻ ድርጊቶቿን በማቆም ወደ ድርድር እንድትመጣ ጥሪዩን አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የየዩክሬን አካል የነበሩ ክልሎች በምርጫቸው ወደ ሩሲያ መምጣት እንፈልጋለን ብለዋል ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ሞስኮ ምርጫቸውን በማክበር ትጠብቃቸዋለች፣ እነዚህን ግዛቶች መንካት ማለት ሩሲያን መንካት ነውም ሲሉ አክለዋል፡፡