ቻይና እና ብራዚልን ጨምሮ ሌሎች የዓለማችን ሀገራት ጉባኤው ሩሲያን ያገለለ ነው በሚል ሳይሳተፉ ቀርተዋል
በስዊዘርላንዱ የዩክሬን ሰላም ስምምነት ላይ ያልፈረሙ ሀገራት እነማን ናቸው?
ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የዩክሬን-ጦርነት እንዲቆም በሚል በስዊዘርላንድ አስተናጋጅነት የዓለማችን ሀገራት የተሳተፉበት የሰላም ጉባኤ ተላሂዷል፡፡
ትናንት ፍጻሜውን ባገኘው በዚህ ጉባኤ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ጨምሮ ከ90 በላይ ሀገራት እንደተሳተፉ ተገልጿል፡፡
የጉባኤው ዓላማ ለዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት መፍትሔ መፈለግ ቢሆንም ጉባኤው ሩሲያን አላካተተም፡፡
ቻይና፣ ብራዚል እና ሌሎች ሀገራት ጉባኤው ሩሲያን ማግለሉ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸው በጉባኤው ላይ በሀገር መሪ ደረጃ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል፡፡
ጉባኤው ትናንት ምሽት ፍጻሜውን ሲያገኝ የዩክሬን ስምምነት የሚባል ሰነድ የጉባኤው ተሳታፊ ሀገራት እንደፈረሙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቡድን 7 አባል ሀገራት እንዳይንቀሳቀስ ከታገደው የሩስያ ገንዘብ 50 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን እንዲሰጥ ወሰኑ
እንደ ዘገባው ከሆነ ይህ ስምምነት ዋና ጨብጡ የዩክሬን ግዛታዊ አንድነት እንዳይሸረሸር እና ሁሉም የዩክሬን ግዛቶች እንዲከበሩ የሚል ነው፡፡
ሳውዲ አረቢያ፣ ሕንድ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት በጉባኤው ላይ በውጭ ጉዳዮች ሚኒስትሮቻቸው በኩል የተሳተፉ ቢሆንም በስምምነት ሰነዱ ላይ ሳይፈርሙ ቀርተዋል ተብሏል፡፡
ብራዚል በዚህ ጉባኤ ላይ በታዛቢነት የተሳተፈች ሲሆን በስምምነቱ ላይ እንዳልፈረመች ተገልጿል፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሰሞኑ ከዩክሬን ጋር የሰላም ስምምነት ለመፈራረም ዩክሬን በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ የተካለሉት አራት ግዛቶች እውቅና ትስጥ፣ ኔቶን ለመቀላቀል የያዘችውን እቅድ ታቁም ሲሉ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡