በግንቦት ወር 35 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን ሩስያ አስታወቀች
ዩክሬን ከምዕራባዊያን ያገኝቻቸው ከባድ የጦር መሳርያዎች መውደማቸውንም የሩስያ ጦር አስታውቋል
ዩክሬን በበኩሏ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ የሞተብኝ ወታደር 31 ሺህ ብቻ ነው ትላለች
በሩስያ እና ዩክሬን መካከል የሚደረገው ጦርነት በግንቦት ወር ብቻ 35 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን ሩስያ አስታወቀች።
ኦክስፋም አሜሪካ የተሰኝው ግብረ ሰናይ ድርጅት ባወጣው መረጃ፣ በጦርነቱ በአማካይ 42 ሰዎች በቀን ህይወታቸው እንደሚያልፍ የገለጸ ሲሆን አጠቃላይ የንጹሀን ሟቾች ቁጥር ደግሞ 10ሺህ 500 ነው ብሏል።
የሩስያ የመከላከያ ሚንስቴር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ በግንቦት ወር ብቻ 35ሺ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡
- ዩክሬን ከአሜሪካ በተለገሱ የጦር መሳሪያዎች ሩሲያን እንድትመታ ተፈቀደላት
- ፑቲን ምዕራባውያን ዩክሬን ሩሲያን በሚሳይል እንድትመታ በመፍቀድ "በእሳት እንዳይጫወቱ" አስጠነቀቁ
ከሞቱት ወታደሮች በተጨማሪ በወሩ ዩክሬን ቁጥራቸው 2 ሺህ 700 የሚሻገር ከባባድ የጦር መሳርያዎች እንደወደሙባትም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር አንድሬይ ቤሎሶቭ አስታውቀዋል።
290 ታንኮች እና ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች እንደወደሙ የገለጹት ሚንስትሩ ከነዚህ መካከል 4 አሜሪካ ሰራሹ አብራም ታንክ፣ 7 የጀርመኑ ሊዮፓርድ ታንኮች እንዲሁም 11 አውሮፕላኖች፣ 4 ሄሊኮፕተሮች እና የሮኬት ማስወንጨፊያ መሳርያዎች እንደሚገኙበት አክለዋል።
የመከላከያ ሚንስትሩ አንድሬይ ቤሎሶቭ እንዳሉት የሩስያ ጦር የዩክሬንን የመዋጋት አቅም ቀስ በቀስ እያዳከመው ነው ብለዋል።
የዩክሬን ጦር በበኩሉ በሳለፍነው የካቲት ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት ሩስያ እንደምትለው በመቶሺ የሚቆጠር የዩክሬን ሰራዊት አልሞተም በሁለት አመቱ ጦርነት የሞቱ ወታደሮች ቁጥር 31ሺህ ብቻ ነው ብሏል። በአንጻሩ ሩስያ 180ሺ ወታደሮች ሞተውባታል ሲል መግለጹ ይታወሳል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ደግሞ በጦርነቱ 70ሺ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን ሲገልጹ 120 ሺህ ያህሉ ደግሞ መቁሰላቸውን ይፋ አድርገዋለ።
በአሁኑ ወቅት በካርኪቭ የሩስያ ጦር ወደ ፊት እየገፋ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ በአንጻሩ ዩክሬን በህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ የተጠናከረ ጥቃት መክፈቷን የሩስያ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በሰኔ አጋማሽ በሩስያ እና ዩክሬን ጉዳይ በሲውዘርላንድ ይመክራል በተባለው የሰላም ጉባኤ ላይ ሞስኮ አልተጋበዘችም፡፡
ለዚህ ምላሽ የሰጠው ክሪምሊን ዩክሬን ከእውነታው ለመሸሽ በጠራችው ጉባኤ ላይ ብንጋበዘም አንገኝም ብሏል፡፡
ሰሞኑን የሩስያው ፕሬዝዳነት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱ አሁን ባለበት ሁኔታ ከዩክሬን ጋር መደራደር እንደሚፈልጉ ያቀረቡትን ጥያቄ አንስቶ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ የጠየቃቸው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልዳይመር ዝለንስኪ የድርድር ጥቄው ‘’ወጥመድ’’ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
ከሩስያ ጋር ምንም አይነት የሰላም ስምምነት የመፈራረም እቅድ እንደሌላቸው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ‘’የእንደራደር ጥያቄው ሞስኮ የጦሯን ሀይል ለማጠናከር ግዜ ለመግዛት ያጠመደችው ወጥመድ ነው’’ ብለዋል።