“የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተው እርምጃ እየወሰዱ ነው”-ጠ/ሚ ዐቢይ
“ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በምእራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
“የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተው ርምጃ እየወሰዱ ነው”-ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ምሽት በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ሀዘን በገለጹበት መግለጫቸው ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልጻለሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ "ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም" ብለው ተነሥተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም የጥፋት ዐቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ እንደሆነ አንስተዋል።
ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የማያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ይህ ተግባርም ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ ታልሞ የሚከናወን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር ነው በሕዝቡ ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱየሚገኙት፡፡ “ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል” ሲሉ የተሰማቸውን ሀዘንም ገልጸዋል።
በመግለጫቸው “ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ” ብለዋል።
“መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል” ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል ብለዋል። “ርምጃም እየወሰዱ ነው” ሲሉም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል ብለዋል።
ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።