ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን በዌምብሌይ እንግሊዝን የምትገጥምበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አንድሬ ሼቭሼንኮን ጨምሮ የቀድሞው የዩክሬን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችም ጨዋታውን በድል ማጠናቀቅ ለዩክሬናውያን ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል
የመጀመሪያ የዩሮ 2024 ማጣሪያ ጨዋታ ያሸነፈው የጋሬዝ ሳውዝጌት ቡድን ለዩክሬን እጅ ይሰጥ ይሆን?
ዩክሬናውያን ዛሬ ከምሽቱ 1 ስአት ጀምሮ ከአመት በላይ የዘለቀውን የጦርነት ሰቆቃ ለተወሰነ ስአትም ቢሆን የሚያስረሳ ሰላማዊ ፍልሚያን በቴሌቪዥን ይመለከታሉ።
የዩሮ 2024 ማጣሪያ ጨዋታ በዌንብሊይ እንግሊዝን ከዩክሬን ያገናኛልና።
የቀድሞው የቼልሲ እና የኤሲ ሚላን ኮከብ አንድሬ ሼቭሼንኮ “እግርኳስ ዩክሬናውያንን አንድ ከሚያደርጉና ከመጥፎ ስሜት ከሚያወጡ ጉዳዮች ቀዳሚው ነው” ይላል።
ጦርነቱ እየቀጠለም የዩክሬን ክለቦች በአውሮፓ መድረክ ውድድራቸውን እንዳላቋረጡ በመጥቀስም የምሽቱ የዌንብሌይ ፍልሚያ በሚሊየኖች ተጠባቂ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።
የባሎንዶር አሸናፊውና ለሀገሩ ዩክሬን 111 ጊዜ ተሰልፎ 48 ጎሎችን ያስቆጠረው ሼቭሼንኮ በለንደን ከሚገኘው ቤቱ ለብሄራዊ ቡድኑ እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዩክሬናያን ሰብአዊ ድጋፍ እያሰባሰበ ይገኛል።
“የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ጠንካራ መሆኑ አያጠያይቅም፤ የኛም (ዩክሬን ብሄራዊ ቡድን) በዚህ ልዩ ቀን የተለየ ብቃቱን ያሳየናል ብዬ እጠብቃለሁ፤ ተጫዋቾቻችን ምንም የሚያነቃቃ ሃይል አያስፈልጋቸውም፤ ሜዳ ላይ የሚገቡት ምን ለማድረግ እንደሆነ ያውቃሉ” በማለትም የድሉን አስፈላጊነት አብራርቷል።
በፈረንጆቹ 1986 የባሎንዶር ሽልማትን የወሰደው ኢጎር ቤላኖቭም ፥”እግርኳስ ዩክሬናውያንን የሚያስተሳስር ሃይማኖት ነው፤ በአውሮፓ የሚገኙ ሰዎች ይህን ለመረዳት ሊከብዳቸው ይችላል፤ በጦርነት ውስጥ በምትገኝ አፍታ ከተራው ዜጋ እስከ ወታደሩ፣ የጤና ባለሙያው እና በጎ ፈቃደኛ ሰራተኛው እግርኳስ የማያይ የለም” ብሏል።
ቢያንስ ለሁለት ስአት ላለፉት 400 ገደማ ቀናት ያሳለፉትን መከራ የሚያስረሳ ነው ያለው ጨዋታ በዩክሬን የበላይነት የመጠናቀቁ ጉዳይ ትርጉሙ ከሶስት ነጥብ በላይ መሆኑንም ያሰምርበታል።
በዛሬው የማጣሪያ ጨዋታ ለመታደም 1 ሺህ ትኬቶች ለዩክሬናውያን እንደሚሰጥና ከ4 ሺህ 200 በላይ የዩክሬን ደጋፊዎች መደበኛ ትኬት መግዛታቸውም ነው የተገለጸው።
እንግሊዝ በጀርመን በሚካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ከጣሊያን፣ ዩክሬን፣ ሰሜን መቄዶንያ እና ማልታ ጋር በምድብ 3 ተደልድላለች።
ከሶስት ቀናት በፊት ጣሊያንን ያሸነፉት ሶስቱ አናብስት ከኳታሩ የአለም ዋንጫ በኋላ በትልቅ መድረክ የመሳተፍ ጉዟቸውን ለማቃናት የዩክሬን ብሄራዉ ቡድንን ዛሬ ምሽት 1 ስአት በዌንብሌይ ይገጥማሉ።
በአንጻሩ ዩክሬን የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን የምታደርግ ሲሆን፥ ከመስከረም ወር 2022 (የአለም ዋንጫ ተሳትፏቸው በዌልስ ከተገታ በኋላ) የመጀምሪያውን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
እንግሊዝ እና ዩክሬን እስካሁን በአምስት አለምአቀፍ ውድድሮች ባደረጓቸው ግጥሚያዎች እንግሊዝ በሁለቱ ስታሸንፍ፥ ዩክሬን አንድ ጊዜ ረታለች፤ ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።