የአውሮፓ ሀገራት ለኑሮ ውድነት ድጎማ 300 ቢሊየን ዩሮ ወጪ ማድረጋቸው ተገለጸ
ሩሲያ የአውሮፓ ህብረት የጣለብንን ማዕቀብ ሳያነሳ ነዳጅ አልክም ብላለች
ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያ፣ ስፔን እና ግሪክ በነዳጅ ዋጋ መናር ክፉኛ የተጎዱ ሀገራት ናቸው ተብሏል
የአውሮፓ ስድስት ሀገራት ለኑሮ ውድነቱ ድጎማ 300 ቢሊየን ዩሮ ወጪ ማድረጋቸው ተገለጸ።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሰባት ወራት ሊሆነው ጥቂት ቀናት የቀሩት ሲሆን ጦርነቱን ተከትሎ የዓለም ነዳጅ እና ምግብ ዋጋ በየዕለቱ እየጨመረ ይገኛል።
ሩሲያ ለአውሮፓ ሀገራት 40 በመቶ የነዳጅ ፍላጎትን የምትሸፍን ቢሆንም ጦርነቱን ተከትሎ ነዳጅ ወደ አውሮፓ እንዳትልክ ማዕቀብ ተጥሎባታል።
በሩሲያ ነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆኑት አውሮፓውያን ደግሞ ታይቶ በማይታወቅ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት እየተጎዱ ሲሆን የዜጎቻቸውን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን በመከተል ላይ ናቸው።
ስድስት የአውሮፓ ሀገራት ብቻ እስካሁን ለሀይል ድጎማ በሚል ያወጡት ገንዘብ 300 ቢሊዮን ዩሮ እንደደረሰ ሮይተርስ ዘግቧል።
እነዚህ ሀገራት ከዓመታዊ መጠባበቂያ በጀታቸው ላይ 23 በመቶውን ለነዳጅ ድጎማ ያዋሉት ሲሆን ጉዳቱ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።
የጀርመን መንግስት ካሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ ለነዳጅ ድጎማ ያወጣው ወጪ 95 ቢሊዮን ዩሮ ሲደርስ ከአውሮፓ ሀገራት በጦርነቱ ከተጎዱ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ሆናለች።
ሌላኛዋ በነዳጅ ዋጋ መናር ከተጎዱ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ፈረንሳይ ስትሆን 67 ቢሊዮን ዩሮ ለነዳጅ ድጎማ ወጪ አድርጋለች ተብሏል፡፡ ይህም በዓመታዊ ምርቷ ላይ የ5 በመቶ ጉድለት እንዲመዘገብ አድርጓል ተብሏል።
ነዳጅን ተጠቅመው ለህብረተሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለሚሰጡ ተቋማት የነዳጅ ድጎማ በማድረጓ 52 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ያደረገችው ሌላኛዋ አውሮፓት ሀገር ደግሞ ጣልያን ናት።
ደቡብ አውሮፓዊቷ ስፔንም ለነዳጅ ድጎማ በሚል 30 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ያደረገች ሲሆን በባንኮች እና ግዙፍ የሀይል ልማት ተቃማት ላይ የግብር ቅነሳ ማድረጓንም አስታውቃለች።
ሆላንድ፣ ግሪክ እና ሆላንድም ዜጎቻቸው በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንዳይጎዱ በሚል እያንዳንዳቸው ከ6 እስከ 10 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ አድርገዋልም ተብሏል።