የአውሮፓ ህብረት የኦሮሚያና የአማራ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እንዳሳሰበው ገለጸ
የአውሮፓ ህብረት ም/ቤት በመንግስትና በህወሓት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ሙሉ ድጋፉን ሰጥቷል
ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ መደበኛ ደረጃ ለማድረስ አዲስና መሰረታዊ መደምደሚያዎችን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል
ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ "መደበኛ" ደረጃ ለማሳደግ ውሳኔ ማሳለፉ ተነግሯል።
የአውሮፓ ህብረት ም/ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳለው ውሳኔው ለህብረቱ እና ለኢትዮጵያ አጋርነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር ለአውሮፓ ህብረት ቁልፍ ስልታዊ አጋር መሆኗን ያሰመረው መግለጫው፤ ህብረቱ ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ሰላም የምታደርገውን ጉዞ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
- የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ተጨማሪ 22 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ ሰጠ
- በአፍሪካ ቀንድ እና በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ ሰላም ለማምጣት የኬንያ ሚና አስፈላጊ ነው ሲል የአውሮፓ ህብረት ገለጸ
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት እና በህውሓት መካከል ጥቅምት 24፤ 2015 ዓ.ም ለተፈረመው "ዘላቂ የጦርነት ማስቆም" የሰላም ስምምነት ሙሉ ድጋፉን ገልጿል።
የስምምነቱን ትግበራ መሰረት በማድረግ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት መደበኛ በማድረግ ወደ ሙሉ እና የተጠናከረ ስልታዊ ግንኙነት እንዲመለስ አደርጋለሁ ብሏል።
ሆኖም ተጠያቂነት እና የሽግግር ፍትህ አስፈላጊ ናቸው ሲል አስምሯል።
የአውሮፓ ህብረት የሽግግር ፍትህ አማራጮችን በማሻሻል ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አበረታታለሁ ማለቱን መግለጫው ጠቅሷል።
ም/ቤቱ በኦሮሚያ፣ አማራ ክልሎችንና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጥቃቶች ህብረቱን በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ግልጽ፣ ሁሉን አቀፍ፣ አካታች እና ህዝብን ያማከለ ብሄራዊ ውይይት እንዲያደርግ አበረታቷል።
በመላው ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር የአውሮፓ ህብረት አቋርጬ ነበር ያለውን "የባለ ብዙ-ዓመት የልማት አመላካች" መርሃ-ግብሩን እንደገና ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።