የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የ81 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ
ትግራይን አንርሳ ያሉት የህብረቱ ፕሬዝዳንት በክልሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ ጠይቀዋል
ድጋፉ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመርዳት የሚውል ነው ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሆን የ 81 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡
ድጋፉ የተጓደሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሻሻል የሚውል ነው ተብሏል፡፡
የህብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል ድጋፉን ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
ቻርለስ ሚሼል ይህን ይፋ ያደረጉት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ነው፡፡
በቆይታቸው በቅርቡ በአውሮፓ እና አፍሪካ ህብረቶች የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ተገናኝተው በተነጋገሩበት ወቅት ያነሷቸው ጉዳዮች የደረሱበትን ደረጃ እንዲሁም በቅርቡ ኮሚሽነር ሌናርሲክ በሀገሪቱ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ መክረዋል።
ሚሼል ለሰብዓዊነት ሲባል የግጭት ማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ መሻሻሉን መመልከታቸውን አንስተዋል።
ይህ መጠናከር እንዳለበት ያነሱት ሚሼል ወደ ክልሉ የሚያስገቡ የየብስ መንገዶች እንዲከፈቱና ስልክን መሰል መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደ ስራ እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም ሩሲያ በዩክሬን ለጀመረችው ጦርነት ትልቅ መዘዝ የሆነውን የምግብ ዋስትናን ለመዋጋት ነዳጅ እና ማዳበሪያ አስቸኳይ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት ያስችላል ያለውን የ633 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል፡፡ ይህን ያስታወሱት የህብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመርዳት የፋይናንስ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ለዚህም የ 81 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋ ያላቸውን ድጋፎች ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ከህወሓት ጋር የተፈጠረውን ችግር በፖለቲካ ደረጃም ሆነ በሰብዓዊነት ደረጃ ለመፍታት መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑ ገልጸውላቸዋል፡፡
ቻርለስ ሚሼልም ይህን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ የሰላም ንግግሮች በተቻለ ፍጥነት እንዲደረጉ አበረታተዋል።
ኢትዮጵያ ለቀጠናው መረጋጋት ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንጻር ለዚህ ሂደት አዎንታዊ ውጤት ለማግኘት የአውሮፓ ህብረት ተስፋ አለውም ነው ሚሼል ያሉት፡፡
በውይይቱ ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እና የኢትዮ ሱዳን ድንበር ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን ግጭቶችን ለመፍታት የውይይት አማራጭን መምረጥ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ህብረቱ በቅርቡ ግድቡን በተመለከተ ያወጣውን መግለጫ ለግብጽ ያደላ ነው በሚል ያወገዘችው ኢትዮጵያ በድጋሚ እንዲያጤነው መጠየቋ ይታወሳል፡፡