“ሙስና በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል እንዲሆን እናደርጋለን”- ኢዜማ
ኢዜማ “ለሀገር በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ” ከየትኞቹም ፓርቲዎች ጋር እንደሚሰራም የፓርቲው መሪ ተናግረዋል
“ለአንድ ዘር/ብሔር የሚሰጥ የተለየ ጥቅም የሚባል ነገር” በአዲስ አበባ ላይ እንደማይኖርም የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ለሀገር በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ከየትኞቹም ፓርቲዎች ጋር እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡
ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን አቋም በተመለከተ ግልጽ ለማድረግ የሚያችል ህዝባዊ ውይይት “የጋራ ህልም፤ የጋራ ከተማ” በሚል መሪ ቃል በማካሄድ ላይ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ “ኢትዮጵያ የመኖር ያለመኖር ጥያቄ ውስጥ ናት” ያሉት የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ “ለሀገር በሚጠቅሙ ጉዳዮች ከአብንም፣ ከባልደራስም፣ ከብልጽግና ጋር እንሰራለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መሪው “ኢትዮጵያ ደህነቷን ለማስጠበቅ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መተባበር” እንደምትችል ነው የተናገሩት “እገዛ ካስፈለገ በይፋ መነገር ነበረበት፤ መብት ግን መነካት” እንደሌለበትም በመጠቆም፡፡
ፕ/ር ብርሃኑ በከተማዋ ላይ ካለው የልዩ ጥቅም ጥያቄ ጋር በተያያዘ “ለአንድ ዘር/ብሔር የሚሰጥ የተለየ ጥቅም የሚባል ነገር የለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ ልትሰፋ እና ልታድግ እንደሚገባ የተናገሩም ሲሆን “በዙሪያዋ ያሉት አርሶ አደሮችም መጠቀም አለባቸው” ብለዋል፡
ሰንደቅ ዓላማን በተመለከተ “በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ አንደራደርም ” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፤ መሐል ላይ አርማ ካስፈለገ በሕዝብ ምርጫና በመነጋገር ብቻ ምላሽ ሊሆን እንደሚችል በማከል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተዘወተረ የመጣውን የከተማ አስተዳደሩን የምክትል ከንቲባ ማዕረግ ሹመት አሰራር ተችተዋል፡፡
“በምክትል ከንቲባ ማዕረግ እየተባለ፣ የሕዝብ ውክልና የሌለው ሰው የሚሾምበት አሰራር ትክክል አይደለም” ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
ከብልጽግና ጋር የተደረገ ውህደት እንደሌለ እና መሠረታዊ ልዩነቶች እንዳሏቸውም ገልጸዋል፡፡
የፓርቲው የሴቶች ጉዳይ ተጠሪ ካውሰር እድሪስ “ሙስና በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል እንዲሆን እናደርጋለን፤ የሃይማኖት አባቶች እንዲያወግዙትም እንጠይቃለን” ሲሉ ተናግረዋል በመድረኩ፡፡