ኢዜማ በመጪው ቅዳሜ የምርጫ ማስጀመሪያ ክንውን እንደሚያካሂድ አስታወቀ
ኢዜማ በ406 ወረዳዎች የሚወዳደሩ እጩዎችን ለይቶ ማዘጋጀቱን ከአሁን ቀደም ማስታወቁ የሚታወስ ነው
ክንውኑ በፓርቲው የምርጫ ዝግጅት ዙሪያ ውይይት የሚደረግበት እና እጩዎች ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በመጪው ቅዳሜ የምርጫ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
መርሃ ግብሩ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ነው ሲሉ ለአል ዐይን የተናገሩት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናዔል ፈለቀ 5 ሺ ሰዎች የሚሳተፉበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ክንውኑ በፓርቲው የምርጫ ዝግጅት ዙሪያ ውይይት የሚደረግበት ነው፡፡
እጩዎች የሚተዋወቁበት እና የፓርቲው አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦች የሚቀርቡበት ነው፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ የጥንቃቄ መንገዶችን ታሳቢ አድርገን የምናካሂደው ነው ብለዋል ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፡፡
ኢዜማ የምርጫ ወረዳን መሰረት ያደረገ 435 ጠንካራ የወረዳ አደረጃጀት መፍጠሩን ከአሁን ቀደም አስታውቋል፡፡
በ406ቱ የሚወዳደሩ እጩዎችን ለይቼ መርጫለሁ ያለም ሲሆን የእጩዎች መመዝገቢያ ቅጽን በየአደረጃጀቱ እየላከ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡
ቀሪዎቹን ወረዳዎች የሚወክሉ እጩዎችን ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ አወዳድሮ አብላጫ ድምጽ በማግኘት የሚያሸንፈውን አስመርጣለሁም ብሏል፡፡
ፓርቲው በምርጫው 2 ሺ እጩዎችን እንደሚያቀርብም ነው አቶ ናትናዔል ለአል ዐይን የተናገሩት፡፡
ኢዜማ ከሰሞኑ ለምርጫ ማስፈፀሚያ የሚሆን 143 ሚለዮን ብር ያስፈልገኛል ብሏል፡፡
ገንዘቡን ለማሰባሰብ የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት መርሃ ግብር በመጪው የካቲት 24 በግሎባል ሆቴል እንደሚያካሂድ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡