15 ሚሊየን ሱዳናዊያን የምግብ ደህንነታቸው አደጋ ውስጥ መሆኑን ተመድ ገለጸ
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የምግብ እጥረቱን እንዳባባሰው ተገልጿል
በሱዳን በግንቦት ወር የዋጋ ግሽበቱ 192 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል
በጎረቤት ሀገር ሱዳን አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድግፍ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግስት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ 15 ሚሊየን ሱዳናዊያን አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ያለው ድርጅቱ እጥረቱን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ችግን እንዳባባሰው ተገልጿል፡፡
በሱዳን ባሳለፍነው ግንቦት ወር ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ በ192 በመቶ እንዳሻቀበ የጠቆመው ድርጅቱ ከውጫዊ ምክንያቶች ባለፈ በሱዳን የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የፖለቲካ ውጥረቱ በሀገሪቱ እየጨመረ ላለው የኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡
የዋጋ ግሽበቱ በዚሁ ከቀጠለም ሚሊየን ሱዳናዊያን በረሀብ ሊሞቱ እንደሚችሉ እና ወደ ከፋ ድህነት የሚገቡ ሱዳናዊያን ቁጥርም ያሻቅባል ሲል ድርጅቱ አሳስቧል፡፡
የዓለም ህጻናት አድን ድርጅት በበኩሉ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ሱዳናዊያን መካከል 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ያህሉ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡
ግጭቶች በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው ዳርፉር ግዛቶች ህጻናት በምግብ እጥረት እየሞቱ እነደሆነ የተገለጸ ሲሆን ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት ሪፖርት ላይ አመልክተዋል፡፡
በሱዳን በተፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት እና የጎሳ ግጭቶች ምክንያት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች እየኖሩ ነውም ተብሏል፡፡
በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በሚመራው የሲቪል አስተዳድር ላይ መፈንቅለ መንግስት መፈጸሙን ተከትሎ በሱዳን የፖለቲካው ውጥረት ተፈጥሯል፡፡
የፖለቲካ ውጥረትን ለመፍታት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ኢጋድ በጋራ የሱዳን ፖለቲከኞችን ለማስታረቅ እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡