በትግራይ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ወደ ምሽት 2 ሰዓት መራዘሙ ተገለፀ
በክልሉ ስራ ላይ ለዋለው አስቸኳይ ጊዝ አዋጅም የአዋጅ መተግበሪያ መመሪያ ማዘጋጀቱም ተገልጿል
የሰዓት እላፊ ገደብ ማሻሻያና የአዋጅ መተግበሪያ መመሪያው ከትላንት በስትያ ጀምሮ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ ሆኗል
በትግራይ ክልል ለአራት ወር ሥራ ላይ በዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገ የሰዓት እላፊ ገደብ ማሻሻያና የአዋጅ መተግበሪያ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
የኮማንድ ፖስቱ አባልና የጊዜያዊ አስተዳደሩ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ንጉሴ በአዋጁ የሰዓት እላፊ ማሻሻያና አስፈላጊነት እንዲሁም በአዋጅ መተግበሪያ መመሪያ ዙሪያ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሀላፊው በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ ያለው ሠላም እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ይበልጥ እንዲነቃቃ በአዋጁ የተደነገገው የሰዓት እላፊ ገደብን ማሻሻል ማስፈለጉን አንስተዋል።
በተለይም በፋብሪካዎችና በግል ተቋማት የሚሰሩ ሠራተኞች ከሥራ ባህሪያቸው አንጻር እስከ ምሽት የሚሰሩ ሰራተኞችን ከግንዛቤ በማስገባት ከምሽቱ 1 ሰዓት የነበረው የሰአት እላፊ ገደብ ወደ ምሽት 2 ሰዓት እንዲራዘም መሻሻሉን አስታውቀዋል ።
ኮማንድ ፖስቱ በክልሉ ስራ ላይ ለዋለው አስቸኳይ ጊዝ አዋጅም የአዋጅ መተግበሪያ መመሪያ ማዘጋጀቱን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
መመሪያው በዋነኛነት የህብረተሰቡን ዕለታዊ እንቅስቃሴ ለመግታት ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አሉባልታ መንዛት፣ የንግድ ተቋማት መዝጋት፣ አድማ ማድረግ ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ ቦታ የመቅረት ክልከላዎችን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።
መመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎች ተላልፈው ሲገኙና ሲፈጸሙ በገንዘብና በእስራት ለመቅጣት የሚያስችል ሆኖ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
የሰዓት እላፊ ገደብ ማሻሻያና የአዋጅ መተግበሪያ መመሪያው ከትላንት በስትያ ጀምሮ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ሀላፊው አስታውቀዋል።